ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፍትሕ ሚኒስትርነት ሲሠሩ የቆዩትን ጌድዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)ን የውጭ ጉዳ ሚኒስትር አድርገው መሾማቸውን አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያስተወቁት ዛሬ ጁመዓ ጥቅምት 8/2017 ነው፡፡
ጌድዮን የተሹሙበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከቀናት በፊት በፊት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ተደርገው በተሠየሙት ታዬ አጽቀሥላሴ የተያዘ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከጌድዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ሹመቶችን ሰጥተዋል፡፡ በዚህም መሠረት የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር ሚንስትር የነበሩት ወይዘሮ ሰላማዊት ካሣን የቱሪዝም ሚንስትር እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሆነው ሲሠሩ የቆዩትን ወይዘሮ ሐና አርአያሥላሴን የፍትሕ ሚንስትር አድርገው ሾመዋል፡፡
ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ2010 ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከተሾሙ ወጣት ሚኒስትሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በፍትሕ ሚኒስተርነት ሹመት ከማግኘታቸው አስቀድሞ ከሠሩበት ፍትሕ ሚኒስቴር በተጨማሪ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሆነው እንዲሁም በሕግ መምህርነት ሠፊ ልምድን ያካበቱ መሆናቸው ይነገራል፡፡
ጌዲዮን ሕግ ካስተማሩባቸው የትምሕርት ተቋማት መካከል አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ሴንትራል ዩሮፒያን ዩኒቨርስቲ፣ ሐዋሳ ዩኒቨርስቲ እና ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ይጠቀሳሉ፡፡ ጌዲዮን ጠሞቴዎስ (ዶ/ር) ለረዥም ጊዜ ባስተማሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ቤት የረዳት ፕሮፌሰርነት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። (ሚንበር ቲቪ)












