Homeዜናና ወቅታዊዜናሐማስ መሪው ያሕያ አስ-ሲንዋር ሠማዕት ሆነዋል አለ

ሐማስ መሪው ያሕያ አስ-ሲንዋር ሠማዕት ሆነዋል አለ

የፍልስጤሙ ሐማስ ያለፉትን ሁለት ወራት በመሪነት የቆዩት ያሕያ አስ-ሲንዋር ሠማዕት መሆናቸውን ያሳወቀው ዛሬ ጁመዓ ነው። ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ እንዳሳወቀው መሪው ሠማዕት የሆኑት በጋዛ ከተማ ውስጥ ባሉበት ነው። ያሕያ አስ-ሲንዋር ሐማስን መምራት የጀመሩት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መገባደጃ እስማኢል ሃኒያህን በመተካት እንደሆነ የሚታወቅ ነው።

በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በተሠራጩ የተንቀሳቃሽ ምስሎች ማየት እንደተቻለው ያሕያ አስ ሲንዋር ከወራሪ የእስራኤል ወታደሮች ጋር በጋዛ ከፍተኛ ትንቅንቅ አድርገው ነው ሠማዕት የሆኑት።

ያሕያ ሲንዋርን ሠማዕት መሆን ይፋ ያደረጉት በጋዛ የሐማስ ቃል አቀባይ ኸሊል ሃያ፤ የያሕያ ሲንዋር እና ከእርሳቸው አስቀድመው ሠማዕትነት የተቀበሉ መሪዎች ለቡድኑ ቀጣይ ትግል ብርታት እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡ ቃል አቀባዩ ጽኑ እና ደፋር ነበሩ ሲሉ የገለጿቸው ያሕያ ሲንዋር እስከ እስትንፋቸው የመጨረሻ ቅጽበት ድረስ ሲፋለሙ እንዳለፉም አረጋግጠዋል፡፡

ጨምረውም ሲንዋር ሕይወታቸውን በሙሉ በትግል ሕይወት እንዳሳለፉ ያስታወሱት ሲሆን፣ በእስራኤል ማጎሪያ ቤቶች ውስጥ በርካታ ዓመታትን በእስር ቢያሳልፉም ወደ ኋላ ከማፈግፈግ ይልቅ በቁርጠኝኘት ትግል መቀጠላቸውንም አውስተዋል፡፡

በ62 ዓመት ዕድሜያቸው ሠማዕት የሆኑት ያሕያ የተወለዱት በኻን ዩኑስ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ እ.አ.አ በ1962 ነበር፡፡ ወላጆቻቸው በጋዛ ሠርጥ ውስጥ በሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለመኖር የተገደደው ከመኖሪያው አሽኬሎን በግዳጅ በመፈናቀሉ ነበር፡፡ የጋዛ እስላማዊ ዩኒቨርሲቲ ምሩቁ በቆይታቸው የዐረቢኛ ሥነ ጽሑፍ አጥንተዋል።

የትግል ሕይወታቸው ገና በወጣትነት በመጀመር ከአምስት ፍልስጤማዊያን ወንዶች ቢያንስ ሁለቱ ያልፉበታል የሚባለውን የእስር ሕይወት የተጋፈጡትም በዚሁ ወቅት ነው፡፡ በ1989 በ27 ዓመት እድሜያቸው በእስራኤል ማጎሪያዎች ታስረው ዕድሜያቸውን በሙሉ በእስር እንዲያሳልፉ ተፈርዶባቸው በርካታ ዓመታትን በእስር ለመቆየት ተገደዋል።

በአጠቃላይ 24 ዓመታትን በእስር ያሳለፉ ሲሆን የተለያየ ዐይነት ስቅይት በሚፈጸምባቸው የእስራኤል ማጎሪያ ቤቶች ውስጥ ዓመታትን ቢያሳልፉም በጽናት በመቆም በቆይታቸው የሒብሩ ቋንቋ ማጥናታቸው ይነገራል። የእስራኤል ባለሥልጣናት ከሦስት ዓመት በፊት በያሕያ ላይ የግድያ ሙከራ ቢያደርጉባቸውም በጋዛ ሆነው ሐማስን እንዲመሩ የተመረጡበት ያን ጊዜ ነበር።

የሐማሱ መሪ በእስር ቤት በነበሩበት ጊዜ የጻፉት “The Thorn and the Carnation” (እሾህ እና አሜከላ) የሚል ርእስ ያለው መጽሐፍ ቅጂ በአሜሪካው ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በኦንላይን ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኝ ነው።

ያሕያ አስ-ሲስዋር፤ በፍልስጤም የነጻነት ትግል ውስጥ ከቤተሰባቸው ብቸኛው ሰው አይደሉም፡፡ ታናሽ ወንድማቸው ሙሐመድ ሲንዋርም እንዲሁ በሐማስ ውስጥ ከፍተኛ አመራር ናቸው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular