ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚሰጠው ሂጅራ ባንክ ሸሪዓን መሠረት ያደረገ “ሐላል ፔይ” የተሠኘ መተግበሪያ በይፋ አስመረቀ። መተግበሪያው የዲጂታል ዋሌት እና ያለማስያዣ ብድር የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል።
ባንኩ መተበሪያውን ይፋ ያደረገው ዛሬ ቅዳሜ ጥቅምት 10/2017 ነው። በአዲስ አበባ ሃያት ሪጀንሲ በተከናወነው መርሐ ግብር ላይ መተግበሪያው የሚሰጠው አገሎግሎት ሸሪዓን መሠረት ያደረገ መሆኑንም በኃላፊዎቹ በኩል አስታውቋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጅ ኢብራሂም ቱፋ፣ የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ጀማል ሙሣ፣ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሠለሞን ደስታ እንዲሁም የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የብሔራዊ ባንክ ምክት ገዥ አቶ ሠለሞን ደስታ፣ በኢትዮጵያ ሸሪዐን መሠረት ያደረገ የፋይናንስ አገልግሎት ዕድገት እያሳየ መምጣቱን ገልጸዋል። በዚህም ከ16 ዓመት በፊት ከወለድ ነጻ አገልግሎት በመስኮት እንዲጀመር መደረጉን በማስታወስ፣ ከአምስት ዓመት በፊት ከወለድ ነጻ አገልግሎት በመጀመሩ የፋይናንስ ዘርፉ በአጠቃላይ ሥፋትና ጥልቀት እያገኘ መምጣቱን አብራርተዋል።
የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ በጠቀሱት የባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መረጃ መሠረት በአሁኑ ሰዓት ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ቁጥር ስምንት ደርሷል። በመስኮት ደረጃ አገልግሎት የሚሰጡት ደግሞ ወደ ሠላሳ ገደማ ነው። በባንኮቹ የተከፈተው ሒሳብ 22.5 ሚሊዮን ሲሆን፣ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 232.71 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በብድር የተሰጠው 104 ቢሊዮን ደርሷል። በብድር የተሰጠው ከግማሽ ያነሰው ነው የተሰጠው ያሉት አቶ ሠለሞን፣ በዚህ ረገድ ሠፊ ሥራ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
አዲስ በመሆኑም የፋይናንስ ብድር ለመስጠት የአገልግሎት ውስንነት፣ የዕውቀት እና ግንዛቤ ችግር አለ ያሉ ሲሆን፣ የሸሪዓ አማካሪ ቦርድ ያልተማከለ መሆኑንና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ ላይ ተግዳሮት በመኖሩ የሂጅራ ባንክ ሐላል ፔይ ቴክኖሎጂን ያማከለ ስለሚሆን ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይገመታል ሲሉ አስረድተዋል። በዚህ ረገድ ፈር ቀዳጅ ሥራ ሠርቷል ላሉት ሂጅራ ባንክ በብሔራዊ ባንክ ሥም ምሥጋና አቅርበዋል።
በመድረኩ ላይ ስለ ሐላል ፔይ ማብራሪያ የሰጡት የኢንፎርሜሽን ሲስተምስ እና ዲጂታላይዜሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ሐሰን ሙሐመድ፣ ሐላል ፔይ ዘመኑን ያገናዘበ አገልግሎት መሆኑን ገልፀዋል። እንደ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አገልግሎቱ አካታችነትን በሠፊው የሚያጠናክር ነው። ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሊጠቀመው ይችላል የተባለው ሐላል ፔይ፣ ወደ ሥራ ለማስገባት ወደ አንድ ዓመት ገደማ ፈጅቷል። በሦስት ወር የሙከራ ጊዜ ከፍተኛ ተቀባይነት በማግኘት ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ደንበኞችን አፍርቷል። ዲጂታል አገልግሎቱ ገንዘብ የመላክ፣ የአየር ሰዓት የመሙላት፣ የዲጂታል ክፍያ፣ የተለያዩ የቢል ክፍያ መፈፀም የሚያስችል ነው። ለኢንተርፕራይዞችም ሸሪዐውን መሠረት ያደረገ ብድር የሚሰጥ ነው። መተግበሪያው ዕቁብ መሰብሰብ እንዲያስችል ተደርጓል። መተግበሪያው በስድስት ቋንቋዎች የሚሠራ ነው።
ሂጅራ ባንክ የማኅበረሰቡን የሥራ ፈጠራ ክሕሎት ይበልጥ ለማጎልበት በተለያዩ የሥራ ዘርፍ ለይ የተሠማሩ የሥራ ፈጠራ ባለቤቶችን አወዳድሮ ያሸልማል ያለውን ሲራራ አዋርድ ይፋ በተመሣሣይ ባለፈው ወር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በነሐሴ 2013 ሥራ የጀመረው ባንኩ፤ በኢትዮጵያ ዕምነቱ ምክንያት ከፋይናንስ ሥርዐቱ እንዲገለል የተደረገውን የሙስሊሙን ማህበረሰብ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመ ነው። (ሚንበር ቲቪ)












