በቱርክ ማኅበረ ፖለቲካ ላይ ተጽዕኗቸው ጉልሕ ነው የሚባሉት የእስልምና መምሕሩ ፈቱላሕ ጉለን፤ በ83 ዓመት ዕድሜያቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ተሰምቷል፡፡ ኅልፈታቸው የሆነው በስደት በሚገኙበት የአሜሪካዋ ፔንሲልቫንያ ግዛት ውስጥ መሆኑም ታውቋል፡፡
ሄርክል የተሰኘው ስለ ፈቱላሕ ጉለን እንቅስቃሴዎች የሚጽፍ ድረ ገጽ እንዳስነበበው ከሆነ፤ የሞቱት በሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እየተከታተሉ ባሉበት ነው፡፡ የሞታቸው ምክንያት እንዲሁም የቀብር ሥነ ሥርዐታቸውን በተመለከተም በቀጣይ መረጃ እንደሚያወጣም ድረ ገጹ አስታውቋል፡፡
እ.አ.አ በ1941 በቱርክ የተወለዱት ፈቱላሕ ጉለን በሀገሪቱ ማኅበረ ፖለቲካ ውስጥ በቀዳሚነት ሥማቸው የተዋወቀው በኢማምነት እንደነበር የሕይወት ታሪካቸው የሠፈራቸው መዛግብት ያመለክታሉ፡፡ ቱርካዊው የቀድሞ ኢማም ኋላ ላይ ወደ እንቅስቃሴ በተቀየረ ድርጅታቸው ሥር የታቀፉ ትምህርት ቤቶችን በመላው ዓለም ከ100 በላይ ሀገራት ውስጥ መክፈት ችለው ነበር፡፡ እነዚህ ትምህርት ቤቶች መሠረታቸውን ካደረጉባቸው ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ ትጠቀሳለች፡፡ ከትምህርት ቤቶች በተጨማሪም አመለካከታቸውን ያራምዱባቸዋል የሚባሉ መጽሔቶችን፣ ጋዜጦችን እንዲሁም የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን በባለቤነት በመያዝ ያስተዳድሩ እንደነበርም ይነገራል፡፡
በሥነ ጽሑፍ ዝንባሌያቸው የሚታወቁት ጉለን፤ መንፈሣዊ ይዘት ያላቸውን በርካታ መጻሕፍትም ለአንባቢያን አድርሰዋል፡፡ ከመጻሕፍቱ መካከል ወደ አማርኛ ቋንቋ የተመለሱ ይኙበታል፡፡
ሙሐመድ ፈቱላሕ ጉለን ሀገራቸው ቱርክ ከወቅቱ ፕሬዝዳንት ሬሲብ ጠይብ ኤርዶጋን ጋር ባላንጣ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ናቸው፡፡ በ1999 ለሕክምና ብለው ከቱርክ በወጡበት ያልተመለሱ ሲሆን፣ በሐምሌ 2016 የተሞከረውን መፈንቅለ መንግሥት በመሪነት አቀነባብረዋል ተብለው በኤርዶጋን የሚከሰሱ ናቸው፡፡ ይህንኑ ተከትሎ በ2017 ቱርክ ዜግነታቸው እንዲገፈፍ አድርጋለች፡፡
ፈቱላህ ጉለን በምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙኃን “መቻቻልን የሚሰብክ” ተብለው የሚወደሱ ቢሆንም፤ ዜግነታቸውን የገፈፈቻቸው ቱርክ፣ ፓኪስታን እንዲሁም የእስላማዊ ትብብር ድርጅት በጥቁር መዝገብ ላይ ያሰፈሯቸው ግለሰብ ናቸው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












