Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችአሜሪካዊያን ሙስሊሞች በምርጫው የቱ ጋ ቆመዋል?

አሜሪካዊያን ሙስሊሞች በምርጫው የቱ ጋ ቆመዋል?

የአፍጋኒስታን የዘር ግንድ ያላት ሴንዝል ሻፌር የምትኖረው በአሜሪካ ቨርጂንያ ግዛት ውስጥ ነው፡፡ ሻፌር ከሠላሳ ዓመታት በላይ ፕሬዝዳንታዊውን ጨምሮ በሀገሪቱ በሚካሄዱ ምርጫዎች ላይ በንቃት ተሳታፊ ሆና ድምጽ ስትሰጥ ቆይታለች፡፡ ሻፌር በነዚህ ምርጫዎች ‘ድምጽሽን ለማን ሰጠሸ?’ ብትሏት፤ ያለማመንታት “ለዲሞክራቲክ ፓርቲ ነዋ” ስትል ትመልሳለች፡፡ አስከትላችሁም ‘በቀጣይ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም ድምጽሽ እንደዚያው ይቀጥላል ወይ?’ ብትሏት ግን ቀድሞ እንደምታደርገው ሳይሆን ለምላሹ ታመነታለች፡፡

ሴንዝል ሻፌር ለምላሽ የምታመነታው በ2017 ኅዳር ወር መገባደጃ በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በዋነኝነት የተፋጠጡት የዴሞራቲክ ፓርቲ እጩዋ ካሚላ ሐሪስም ሆነ የሪፐብሊካን ፓርቲው ዶናልድ ትራምፕ ምርጫዎቿ ስላልሆኑ ነው፡፡ ሻፌር ሁለቱም ቀርተው ሦስተኛ የልቧን የሚሞላ ፓርቲ ቢኖር ትመርጣለች፡፡ ሴንዝል ሻፌር እስካዛሬ ድረስ ስትመርጠው የቆየችው ዴሞክራቲክ ፓርቲ ላይ ‘ለምን ፊትሽን አዞርሽ?’ የሚል ጥያቄ ቢሰነዘርላትም ምክንያት አላት፡፡ ባለፈው ምርጫ ድምጽ የሰጠቻቸው ፕሬዝዳንት ባይደን የጋዛን ጉዳይ የያዙበትን መንገድ እንዳልወደደችው ለቮይስ ኦፍ አሜሪካ ጋዜጠኞች ተናግራዋለች፡፡

በአሜሪካ ምርጫ ሴንዝል ሻፌር የያዘችው አቋም የበርካታ ሙስሊሞችን አስተሳሰብ የሚወክል መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ሙስሊም አሜሪካዊያን በቀጣይ ምርጫ ዋንኛ ጉዳያቸው ጋዛ ሆናለች፡፡ ሙስሊም መራጮች ቀጣይ ፕሬዝዳንታቸውን የሚመዝኑት በጋዛ ላይ በሚይዙት አቋም ላይ ተመሥርተው ነው፡፡ ሆኖም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ስለ ጉዳዩ የሚናገሩ ሙስሊም አሜሪካዊያን ነገሩ ግራ አጋቢ እንደሆነባቸው ያስረዳሉ፡፡ የቨርጂንያ ግዛት ነዋሪዋ የቴክኖሎጂ ባለሞያ ሴንዝል ሻፌር፤ ይህ ምናልባትም “በዚህ ወቅት የምወስነው ፈታኙ ውሳኔ ነው” ማለቷም ለዚህ ነው፡፡  

ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከሦስት ወር ያነሰ ጊዜ በቀራት አሜሪካ፤ የሙስሊሞች አሐዝ የአጠቃላይ ሕዝቡን 1 በመቶ ብቻ የሚይዝ ነው፡፡ ነገር ግን በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ሙስሊሞች ነዋሪነታቸው በሀገሪቱ ምርጫ ውስጥ ተጽዕኗቸው በሚጎላ ግዛቶች ውስጥ በመሆኑ ድምጻቸው የሚናቅ አይሆንም፡፡ እነዚህ ግዛቶች ሚቺጋን፣ ዊንኮንሲን፣ አሪዞና፣ ጆርጂያ፣ ኔቫዳ እና ፔንሲልቫንያን ያጠቃልላሉ፡፡ በአሜሪካ ምርጫ ላይ ጉልህ ተጽዕኖ በሚያሳርፉት በእነዚህ ግዛቶች የሚኖሩ ዜጎች ድምጽ፤ እንደሌሎች ግዛቶች ሁሉ ቀድሞ መላ ምት ሊሰጥበት የሚችል ቢሆንም በርግጠኛነት አሸናፊውን ለመተንበይ የሚያስቸግሩ ናቸው ይባልላቸዋል፡፡ በዋነኝነት ካማላ ሐሪስን እና ትራምፕን በሚያፋጥጡት በእነዚህ ግዛቶች ውስጥ የመራጮች ድምጽ እንደ ሁኔታው ሲዋልል ይስተዋላል፡፡ በቀጣይ ምርጫም ቢሆን በግዛቶቹ ካማላ ሐሪስ ያሸንፉ አልያም ትራምፕ ርግጠኛ ሆኖ የሚናገር የለም፡፡

ለምሣሌ በአሜሪካ በርካታ የሙስሊም ቁጥር እንዲሁም የሙስሊም ባሕል በሥፋት ይንጸባረቅበታል በሚባልበት በሚቺጋን ግዛት፤ በምርጫው ካማላ ሐሪስ 48 በመቶ ድምጽ፣ ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ 43 በመቶ ድምጽ ያገኛሉ ተብሎ ቅድመ ግምት ቢቀመጥም ቁጥሩ አሁንም ከትንበያ ሊያልፍ የሚችል አይሆንም እየተባለ ነው፡፡

ይህን የሚያጸና የሚመስለው የሕዝብ አስተያየት ባለፈው ሳምንት ይፋ ተደርጓል፡፡ አዲሱ የሕዝብ አስተያየት ከላይ የተዋወቅናትን የቨርጂንያ ግዛት ነዋሪዋን ሴንዝል ሻፌርን አቋም የሚያንጸባርቅ ሆኗል፡፡ ካውንስል ኦን አሜሪካን ሪሌሽንስ ይፋ ያደረገው የሕዝብ አስተያየት እንደሚያሳየው፤ በምርጫው ዐይነተኛ አማራጭ እያሰሱ የሚገኙት ሙስሊሞች ከሁለቱ ተመራጮች ውጪ አዲስ ሥም አስገብተዋል፡፡

እኚህ ሰው አረንጓዴ ፓርቲን የሚወክሉት ጂል ስቴይን ናቸው፡፡ ስቴይን የሚመሩት አረንጓዴ ፓርቲ በመሠረቱ እንደ ሥያሜው ለአካባቢ ጥበቃ የቆመ ነው፡፡ በአካባቢ ጥበቃ ስለ ማኅበራዊ ፍትሕ የሚሟገተው ፓርቲ፤ አመጽ እና ጦርነትን ይቃወማል፡፡ በዚሁ አግባብ የፓርቲው መሪዎች የጋዛ ጦርነት ማብቃት አለበት የሚል አቋም በመያዝ ይታወቃሉ፡፡ አቋም መያዝ ብቻ አይደለም፤ አደባባይ ወጥተው ሲሟገቱም ይታያሉ፡፡

የሙስሊም መራጮች የሕዝብ አስተያየት ይፋ ሲደረግ የ74 ዓመት እድሜ ያላቸው ጂል ስቴን፤ የ54 ዓመት እድሜ ካላቸው የዴሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩዋ ካማላ ሐሪስ ጋር እኩል 29 በመቶ ድምጽ ያገኙትም ለዚሁ ይመስላል፡፡ ከሕዝብ ድምጹ ጋር በተገናኘ ለሚድል ኢስት ዐይ የተናገሩት የግሪን ፓርቲ ዕጩው ጂል ስቴይን፤ የጋዛ ጭፍጨፋ ከሙስሊም መራጮች ጋር ተመሳሳይ አቋም እንዲይዙ ማድረጉን በማስታወስ፤ ድጋፍ ማግኘታችንም አስደስቶናል ብለዋል፡፡ ሆኖም ተንታኞቹ እንደሚሉት አረንጓዴ ፓርቲ በምርጫው ዐይነተኛ ሚና አይኖረውም፤ አረንጓዴ ፓርቲ በአሜሪካ ምርጫ እንደ አሯሯጭ ነው፡፡ ስለዚህ ኩርፊያን ለማንጸባረቅ ካልሆነ ፋይዳ አይኖረውም፡፡

በሕዝብ አስተያየቱ ሌላኛው ተመራጭ ካማላ ሐሪስ፤ በሚያደርጓቸው ንግግሮች በፍልስጤማዊያን እና ጋዛ ጉዳይ ሐዘኔታ የሚያሳዩ ይመስላሉ ቢባልም፤ በተመሳሳይ እንደ ባልንጀራቸው ጆ ባይደን ሁሉ ጋዛ ላይ ቦንብ የምታዘንበውን እስራኤልን በጦር ከማስታጠቅ የሚመለሱ አይደሉም በሚል ነቀፌታ የሚሰነዝርባቸው ናቸው፡፡ ካውንስል ኦን አሜሪካን ሪሌሽንስ ባወጣው የሕዝብ አስተያየት መለኪያ መሠረት የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ፤ ውዝግብ በማሳደድ የሚታወቁት ዶናልድ ትራምፕ፤ በሙስሊም መራጮች ያገኙት ድምጽ 11 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ትራምፕ ለፍልጤማዊያን ምንም ዐይነት ሐዘኔታ አያሳዩም በሚል ተደጋግመው የሚተቹ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በ2016 ምርጫ እስልምናን እና ሙስሊሞችን በሚመለከት የሠነዘሩት ፀያፍ አስተያየት ሙስሊም መራጮች ፊት እንዳይሰጧቸው አድርጓቸዋል፡፡

በ2020 በተካሄደው የሀገሪቱ ምርጫ አሜሪካዊያን ሙስሊሞች ለምርጫው መሥፈርት አድርገው ካስቀመጧቸው ጉዳዮች መካከል ቀዳሚ የነበረው የጤና ጉዳይ ነበር፡፡ ሙስሊም መራጮች በጤና ጉዳይ የተሻለ ፖለሲ ለሚያቀርብ ቀዳሚውን ድምጽ ሲሰጡ፣ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በተከታይነት አስቀምጠዋል፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የመራጮቹ መሥፈርት ሆኖ አልፏል፡፡

በቀጣይ ለሚካሄደው ምርጫ በጆርጂያ፣ ሚቺጋን እና ፔንሲልቪንያ ግዛቶች በምርጫው ከሚሳተፉ ሙስሊሞች መካከል 61 በመቶው በጋዛ ጉዳይ የተሻለ ፖሊሲ አለው ለሚሉት ዕጩ ድምጻቸውን መስጠት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ አሜሪካዊያኑ ሙስሊሞች ሌሎች የሀገራቸው ጉዳዮች ከፍልስጤማዊያን ሕልውና እንደማይበልጥም አረጋግጠዋል፡፡

በዚህ መሃል በሙስሊም መራጮች በ2016 ዐይንህ ላፈር የተባሉት ዶናልድ ትራምፕ፤ በተለይ የዐረብ ግንድ ያላቸውን ሙስሊም መራጮች ድምጽ ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸው አልቀረም፡፡ ትራምፕ የሙስሊም መራጮችን ልብ የሚራራልኝ ከሆነ በሚል በታዋቂው ሊባኖሳዊ የሴት ልጃቸው ባለቤት፤ አማቻቸው ማሳድ ውሎውስ በኩል የሚቺጋን ግዛት ሙስሊሞችን እያባበሉ ይገኛሉ፡፡ ትራምፕ ሙስሊሞችን ድምጽ ስጡኝ የሚሉት፤ የባይደን አስተዳደር ለጋዛ ጉዳይ መፍትሔ ማምጣት አቅቶታል የሚል መከራከሪያ በማቅረብ ነው፡፡ ይህን የትራምፕ ድራማ እንደ ሻፌር ዐይነት በምርጫው ከሠላሳ ዓመታት በላይ የተሳተፉትም ሆነ የአዲሱ ትውልድ አሜሪካዊያን ሙስሊሞች በንቃት መከታተላቸው የአደባባይ እውነት ነው፡፡ የአሜሪካ ሙስሊሞች ኅዳር 2017 እስኪደርስ ድረስ ሌሎች ድራማዎችንም መመልከታቸው የሚቀር አይመስልም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular