እ.አ.አ ሰኔ 6/212 – እለተ እሑድ፡፡ ግብጽ በአብዮት ማግሥት ቆማለች፡፡ ሕዝቧም በመጨረሻ ዘመናቸው ‹‹አምባገነን›› ሲላቸው የነበሩትን ጠንካራውን ሰው ሆስኒ ሙባረክን ጥሎ ምርጫ ደግሶ ውጤቱን እየተጠባበቀ ነው፡፡ የምርጫው ውጤት ይፋ ሲደረግ ሀገሩ ሁሉ ድብልቅልቁ ወጣ፡፡ የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲው ሙሐመድ ሙርሲ የድግሱ ተመራጭ ሰው ሆኑ፡፡
ለምርጫው ከግብጽ ሕዝብ ለምርጫ 26 ሚሊዮኑ ተመዝግቦ ነበር፡፡ ሙርሲ ከነዚህ ውስጥ የ13.2 ሚሊዮኑን ይሁንታ አገኙ፡፡ የምርጫውን ውጤት ይፋ መደረግ ተከትሎ እሑድ ምሽቱን ሙሐመድ ሙርሲ በግብጽ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ድምጽ ለሰጣቸው የሀገራቸው ሕዝብ ምሥጋና አቀረቡ፡፡ መራጮቻቸውን ‹‹የኔ ቤተሰብ›› እና ‹‹ተወዳጆቹ›› በሚል ቅጽል የጠሩት ሙርሲ፤ ‹‹የተነጠቀውን መብታችሁን አስመልሳለሁ›› ሲሉ ቃል ገቡ፡፡ በዚህ ብቻ አላበቁም፤ ‹‹እኔ መብት የለኝም፤ ያለብኝ ኃላፊነት እናንተን በሥርዐት የማስተዳደር ብቻ ነው›› አሉ፡፡ ‹‹ኃላፊነቴን ካልተወጣሁ አለመታዘዝ መብታችሁ ነው›› ያሉትም በዚሁ ንግግር ነበር፡፡
የሙሐመድ ሙርሲ አሸናፊነት ሲታወጅ ቀድሞ ለተቃውሞ አገልግሎት ሲውል የቆየው ዝነኛው የካይሮ አደባባይ ታህሪር፤ በሕዝብ ማእበል ተጥለቀለቀ፡፡ የግብጽን ሰንደቅ አላማ ያነገቡ ዜጎች ደጋግመው የሚያሰሙት የደስታ ድምጽም በተክቢራ የታጀበ ሆነ፡፡ ዜጎቻቸውን በደስታ የሞሉት ሙርሲ፤ ከዓለም ሀገራት ‹‹የእንኳን ደስ አለህ›› መልእክት ጎረፈላቸው፡፡ ለደስታ መልእክቱ ቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ፍልስጤም ቀዳሚዎቹ ሆኑ፡፡ አሜሪካም የሙርሲን ድል አወድሳ መግለጫ አወጣች፡፡ እስራኤል በአንጻሩ ‹‹እንግዲህ ምን ማድረግ ይቻላል›› በሚል ድምጸት፤ በቤንያሚን ኔታንያሁ በኩል ‹‹ውጤቱን መቀበል ግድ ነው›› አለች፡፡
በዚህ ጊዜ ሁሉም በሙርሲ የተሸነፈ መሰለ፡፡ በሆስኒ ሙባረክ ዘመን ግብጾቹ ‹‹የጠፋው ትውልድ›› ሲሉ የሚጠሩትን የፖለቲካ የበይ ተመልካች ነው የሚባልለትን ትውልድ ወካይ ተደርገው የሚወሰዱት ሙርሲ፤ ማሸነፋቸው ከሙስሊም ወንድማማቾች ጎን ለጎን ለዓመታት በማኅበረሰብ ግልጋሎት የማሳለፋቸው ውጤት ነው ተባለላቸው፡፡ የሙርሲ ማሸነፍ አምባገነነትን አጥብቆ የመፀየፍ ምልክትም ተደርጎ ተወሰደ።
ከዚህ ክስተት በኋላ አንድ ዓመት ወደፊት እንንደርደር። እ.አ.አ ሐምሌ 14/2013 ደርሰናል፡፡ በዚህ ቀን ሙርሲ ለአንድ ዓመት ከጥቂት ቀናት የቆየው የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን ማብቂያ ላይ ደረሱ፡፡ ሙርሲ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ተደረገ፡፡ ነገሩ ሁሉ የተከሰተው በፍጥነት ነበር፡፡ የጉዳዩ ዋና ተዋናይ ሆነው ብቅ ያሉት በራሳቸው በፕሬዝዳንት ሙርሲ የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ተደርገው የተሾሙት ወታደሩ ዓብዱልፈታህ አልሲሰ ናቸው፡፡ የ58 ዓመቱ አል ሲሲ፤ በሙርሲ ሥልጣን ዘመን በተለይ ወደማብቂያው ሲያጉረመርሙ ነበር፡፡ ከአሜሪካ ሠራዊት እና የሀገሪቱ ጀነራሎች ጋር ወዳጅ የሆኑት ሰው፤ ከአንድ ዓመት ያልዘለለ የሥልጣን እድሜ ያላቸውን ሙርሲን ሕዝብን ቅር ስላሰኙ፤ ምንም እንኳ ጦሩ በእንደዚህ ዐይነት ጉዳይ ጣልቃ መግባት ባይችልም ‹‹ሀገራችንን ለማዳን እንገደዳለን›› ብለው ሥልጣን ፈነቀሉ፡፡
በአሜሪካ ፔኒስልቪንያ የጦር ኮሌጅ የወታደራዊ ሳይንስ ለአንድ ዓመት ያጠኑት ሲሲ፤ ለቦታው የሾሟቸውን፤ በምርጫ ያሸነፉትን ሙሐመድ ሙርሲን በቤታቸው የቁም እስር ላይ እንዲቆዩ አደረጉ፡፡ ጥቂት ቆይተው ደግሞ እስር ቤት ወረወሯቸው። ነገር ግን የአል ሲሲ ውሳኔ ከአንድ ዓመት በፊት ሙርሲን በእልልታ ለተቀበሏቸው ደጋፊዎቻቸውና ለግብፃዊያን ዴሞክራሲ ናፋቂዎች የሚዋጥ አልሆነም፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት ደስታ ያስተናገዱ ጎዳናዎች በተቃውሞ ይናጡ ጀመር፡፡ አንዱ ሌላውን እየጠራ የራቢዓ እና የአል ናህዳ አደባባዮች ሰው ሞላቸው፡፡ ቀን፣ ቀናትን እየወለደ ሳምንት ሞላ፡፡ ሳምንቱ ሌላ ሳምንት አስከተለ፡፡ ከዚያው ወር ሆነ፡፡ በጎዳና ውሎ ማደር፤ እዚያም መብላት እና መስገድ የሰላም እና ዴሞክራሲ ዘቦቹ ሥራ ሆነ፡፡ በዚህ መንገድ ስድስት ሳምንታት ተቆጠሩ፡፡ ግብጻዊያን ትንቅንቅ ውስጥ የገቡት ‹‹ሀገራችንን ፈቅደን ከመረጥነው ሰው ወታደሩ አይቀማንም›› በሚል ነበር፡፡ ፍጥጫው እየተካረረ ሄደ፡፡ ግብጻዊያኑ አደባባይ መዋላቸው እየጨመረ ሲመጣ፤ የሀገሪቱ ጀነራሎች ጎን ለጎን የሚያዘንቡት ማስፈራሪያም በድምጸት ከፍ አለ፡፡ በርግጥ አንዳንዶቹ ጀነራሎች ሕዝቡን ቀስ በቀስ ከአደባባዮች ላይ እንዲበተን እናደርገዋለን እያሉ ሲናገሩ ነበር፡፡ የራቢኣ እና አልናህዳን ጎዳናዎች የሞሉት ግብጻዊያን ቁጥር 85 ሺሕ ሲደርስ ግን የወታደሩ ቃል እና ተግባር ለየቅል ሆነ፡፡
በዚሁ እለት ረፋድ አካባቢ አሳዛኙ ድርጊት ተከተለ። የግብጽ ፀጥታ ኃይሎች ሕፃን አዋቂ ሳይመርጡ ንጹሐን ደረት ላይ መተኮስ ጀመሩ፡፡ የራቢዓ እና አልናህዳ ጎዳናዎችንም በደም ጨቀዩ። በአንድ ቀን ብቻ እነዚሁ ፀጥታ ኃይሎች ቢያንስ 900 የሀገራቸውን ዜጎች ያለ ርህራሄ ገደሉ፡፡
ክስተቱ 11 ዓመቱን የደፈነው በዚህ ሳምንት ነው፡፡ ስለ እለቱ በምልሰት የሚጽፉ ክስተቱን የራቢዓ ጭፍጨፋ በማለት ይጠሩታል፡፡ በግብጽ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ታይቶ አይታወቅም የሚባለው ይህ ጭፍጨፋ ሲፈጸም በሥፍራው የነበረችው ግብጻዊቷ ጂሃን ማሂር አቅል፤ ‹‹በሕይወቴ እንዲህ ያለ ቀን ገጥሞኝ አያውቅም›› በማለት ቀኑን ታስታውሰዋለች፡፡ ጂሃን በእለቱ በጎዳናዎቹ ዐይን አሻግሮ መመልከት እስከሚችለው ድረስ ቢያማትር የሚመለከተው ደም ብቻ እንደነበርም ለሚድል ኢስት ዐይ ጋዜጠኞች ተናግራለች፡፡ ‹‹በፍጹም እተርፋለሁ ብዬ አልገመትኩም ነበር›› ባለችበት ቀን፣ የሀገሯ ወታደሮች ‹‹ጥይት አዘነቡብን›› ብላለች፡፡

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ በዚህ ክስተት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 817 ነው ብሏል፡፡ ጭፍጨፋውን የፈጸመው የአል ሲሲሰ አስተዳደርም ግድያውን የሚመረምር ኮሚቴ አቋቁሞ ነበር፡፡ ኮሚቴው አረጋገጥኩት ያለው የሟቾች ዐሐዝ ከመብት ተሟጋች ድርጅቱ ያነሰ ነው፡፡ ቁጥሩ ቢለያይም ከሪፖርቱ በኋላ በጭፍጨፋው ላይ የተሳተፈ አንድም ግለሰብ ለፍርድ ሲቀርብ አልታየም፡፡ ፍትሕ ናፋቂ ግብጻዊያንም በዲሞክራሲያዊ መንገድ የመረጧቸው የሙስሊም ወንድማማቾቹ ታማኙ ሰው ሙሐመድ ሙርሲ በፍርድ ቤት ተዝለፍልፈው ወድቀው ሲሞቱ መመልከት ዕጣቸው ሆኗል፡፡ የግብጻዊያን የዴሞክራሲ ተስፋም እንደ ጉም ሳይተን አልቀረም፡፡
በርግጥ ወደ አንድ ሺሕ የሚጠጉ ግብጻዊያን በራቢኣ እና አልናህዳ አደባባዮች ከረገፉ አስራ አንድ ዓመታት በኋላ፤ የሀገሬውን አንዳንድ ሰዎች ስለ ክስተቱ ብስታስታውሷቸው ጉዳዩን የዘነጉት ሊመስል ይችላል፡፡ ለዚህ ዋንኛው ምክንያቱ ደግሞ የዓብዱልፈታህ አል ሲሲ ዘመን ኑሮ ነው፤ ግብጻዊያን በዓብዱልፈታህ አል ሲሲ አስተዳደር ዐይተውት የማያውቁትን ችጋር እየተጋፈጡ ነው፡፡ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የተመለከቱ ሪፖርቶችን ላነበበ፤ በግብጽ ቀድሞ መካከለኛ ኑሮ ይኖሩ ነበሩ የሚባሉ ሰዎች፣ ወደ ድኽነት መደብ መውረዳቸውን ይታዘባል፡፡ ድኾች ደግሞ፤ የድኻ ድኻ ሆነዋል፡፡ ሙሐመድ ሙርሲን በግፍ በሸኘችው ግብጽ፤ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ አልበቃ ብሏቸው ምሳ ሳይበሉ መዋል ከጀመሩም ሰነባብተዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












