የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) ምርጫ፤ በቀጣዩ ዓመት 2017 መጨረሻ ላይ እንደሚካሔድ የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ሸይኽ ሐሚድ ሙሣ ተናገሩ፡፡ ዋና ጸሐፊው በሁሉም እርከን ለሚገኙ የምክር ቤቱ ኃላፊዎች በምርጫው ኃላፊነታቸውን “ለተተኪው ለማስረከብ” ራሳቸውን ዝግጁ እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡
የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ሸይኽ ሐሚድ ሙሣ፤ ከሦስት ሳምንታት በኋላ በሚጀምረው አዲስ ዓመት የመጨረሻ ጊዜያት ምርጫ እንደሚካሔድ የተናገሩት በክብር እንግድነት በተገኙበት የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው፡፡ ትናንት ሐሙስ ነሐሴ 9/2016 በተከናወነው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ስለ ምርጫው የተናገሩት ዋና ጸሐፊው፤ ምርጫው የሚካሔደው በ2017 መጨረሻ ላይ እንደሚሆን ከመጠቆም ውጪ ትክክለኛውን የጊዜ ሠሌዳ አልገለጹም፡፡
ሸይኽ ሐሚድ ሙሣ በንግግራቸው ምርጫው በሚደርስ ጊዜ “አልመርጥም፣ አላስመርጥም” እንዲሁም “አለቅም” ማለት አይገባም በማለት በወረዳ፣ በክፍለ ከተማ እና በከተማ ደረጃ ላሉ አመራሮች ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ “የወንበሩ ሙቀት እንዳይሰማን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ዓመት ምርጫ ያካሔዳል የተባለው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ የወቅቱ ኃላፊዎች ወደ ሥልጣን ከመጡ ባለፈው ወር ሐምሌ ሁለት ዓመት ሞልቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ለአመራሮቹ የሰጠው የሥልጣን ጊዜ ሦስት ዓመት ነበር፡፡ ፕሬዝዳንቱ ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም መጋቢት 10፣ 2016 ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮችና ከክልሎች ከመጡ አባቶች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በአዲስ አበባ ባደረጉት ውይይት ላይ አንስተውት ነበር፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረው ውይይት ላይ ስለ ምርጫ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም፤ ጊዜው ሲደርስ “ከሕዝብ ነው የተረከብነው፤ ለሕዝብ እናስረክባለን” ሲሉ ተደምጠው ነበር፡፡ አክለውም በአሁኑ ሰዓት መንግሥት ከመጅሊስ ላይ “መቶ በመቶ እጁን አንስቶ” በነጻነት እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በቀጣይ ምርጫ መንግሥት እንዲያግዛቸው ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ፕሬዝዳንቱ ይህን ጥያቄ ባቀረቡበት ጊዜ “ጣልቃ ገብ እንድትሆኑ” አይደለም ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ እንደ መንግሥት መጪው ምርጫ ላይ አግዙን የምንለው “አስፈላጊ ነገሮችን ሁሉ እንድታመቻቹልን ነው” በማለት ከመንግሥት የሚፈልጉትን እገዛ አብራርተው ነበር፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












