የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ በከተማው አስተዳደር አዲስ ሹመት ላገኙት አቶ ኻሊድ ሙሐመድ ሽኝት አደረገ፡፡ ምክር ቤቱ የቀድሞ ባልደረባውን በሸኘበት በዛሬው ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ እያካሔደ ይገኛል፡፡
ምክር ቤቱ ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 9/2016 ለቀድሞ ባልደረባው ኻሊድ ሙሐመድ ሽኝት ያደረገው፤ በአዲስ አበባ ከተማ ኤሊያና ሆቴል እያካሔደ በሚገኘው ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤው ነው፡፡
በዛሬው እለት ሽኝት የተደረገላቸው አቶ ኻሊድ ሙሐመድ፤ ሽኝት የተደረገላቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ቢሮ ውስጥ አዲስ ኃላፊነት ስለተረከቡ ነው፡፡ “ሚንበር ቲቪ” ከጉባዔው እንደሰማው፤ አቶ ኻሊድ ሙሐመድ በከተማው አስተዳደር የኮሚኒኬሽን ቢሮ ውስጥ የምክትል ቢሮ ኃላፊነት ሹመት አግኝተዋል፡፡

አቶ ኻሊድ ሙሐመድ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ አዲስ ሹመት ከማግኘታቸው አስቀድሞ ያለፉትን ዓመታት በቆዩበት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ውስጥ በመጨረሻ ዘመን የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ሲሠሩ ነበር፡፡ ከዚህ ኃላፊነት በፊት ደግሞ የምክር ቤቱ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ የቀድሞው የምክር ቤቱ ባልደረባ በአሁኑ ሰዓት በአዲሱ ኃላፊነት በሥራ ላይ እንደሚገኙም ታውቋል፡፡
የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በጋዜጠኝነት ያገኙት አቶ ኻሊድ ሙሐሙድ፤ በከተማው የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ውስጥ ከመሥራታቸው በፊት በተማሩበት የጋዜጠኝነት ሞያ ይታወቁ ነበር፡፡ በዚህም በዋነኝት የሙስሊሙ ጉዳዮች ላይ አተኩረው በሚሠሩ መገናኛ ብዙኃን ሠርተዋል፡፡ አቶ ኻሊድ ሙሐመድ በሁለተኛ ዲግሪ በሁለት የትምህርት ዐይነቶች ተመርቀዋል፡፡ የቀድሞው ጋዜጠኛ በመጀመርያ የተማሩት ግሎባል ስተዲስ ኤንድ ኢንተርናሽናል ሪሌሽን ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ በአመራር ተመርቀዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












