Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችያሕያ አስ-ሲንዋር ማን ናቸው?

ያሕያ አስ-ሲንዋር ማን ናቸው?

የፍልስጤሙ ሐማስ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ሰማዕት የሆኑትን እስማኢል ሃኒያህን ለመተካት ባካሄደው ሹራ፤ አዲሱን መሪውን ይፋ አድርጓል፡፡ ሐማስ ለሁለት ቀናት በኳታር ዶሓ ባካሄደው ዝግ ሹራ ቀጣዩ መሪ ያሕያ አስ-ሲንዋር እንዲሆኑ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡ ለሁለት ቀናት የተከናወነው የቡድኑ ሹራ ሲጠናቀቅ ይፋ የተደረገው ሥም የእስራኤል እና ምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃንን ያርበደበደ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

ለመሆኑ እስማኢል ሃኒያህን የተኩት ያሕያ አስ-ሲንዋር ማን ናቸው?

የያሕያ አስ-ሲንዋር የልጅነት ሕይወት ታሪክ፤ ከሳምንት በፊት የተለዩትን የእስማኢል ሃኒያህ ግልባጭ የሚመስል ነው፡፡ እስማኢል ሃኒያህ የተወለዱት በስደተኞች መጠለያ ውስጥ ነበር፡፡ ያሕያ አስ-ሲንዋርም በተመሳሳይ የተወለዱት በኻን ዩኑስ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ እ.አ.አ በ1962 ነው፡፡

የያሕያ ቤተሰብ ልክ እንደ ሃኒያህ ሁሉ በወቅቱ በጋዛ ሰርጥ ውስጥ በሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለመኖር የተገደደው፤ ከመኖሪያው አሽኬሎን በግዳጅ በመፈናቀሉ ነበር፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ትምሕርታቸውን የተከታተሉትም በተመሳሳይ ተቋም ውስጥ ነው፡፡ እስማኢልም ሆነ ያሕያ የጋዛ እስላማዊ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ናቸው፡፡ ሁለቱም የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ያጠናቀቁት በዐረቢኛ ሥነ ጽሑፍ ነው፡፡

ከዚህ በኋላ ያለው የሁለቱ ታጋዮች የሕይወት መንገድም ቢሆን በተለያየ አጋጣሚ የተሞላ ቢሆንም፤ መዳረሻው አንድ ሆኗል – ነጻነት፡፡ ሐማስን እንዲመሩ የተመረጡት ያሕያ አስ-ሲንዋር፤ የትግል ሕይወታቸው የተጀመረው ገና በወጣትነት ነበር፡፡ ወጣቱ ያሕያ ከአምስት ፍልስጤማዊያን ወንዶች ቢያንስ ሁለቱ ያልፉበታል የሚባለውን የእስር ሕይወት የተጋፈጠው በዚሁ ወቅት ነው፡፡ ያሕያ በ1989 በ27 ዓመት እድሜው በእስራኤል ማጎሪያዎች ታስሮ ዕድሜውን በሙሉ በእስር እንዲያሳልፍ ተፈርዶበት በርከት ያሉ ዓመታትን በእስር ቆይቷል፡፡

ወጣቱ ያሕያ አስ-ሲንዋር ከእስር ቤት ሲመለስ ወደ ጎልማሳነት ተሻግሮ ነበር፡፡ በአጠቃላይ 24 ዓመታትን በእስር ያሳለፉት ያሕያ፤ የተለያየ ዐይነት ስቅይት በሚፈጸምባቸው የእስራኤል ማጎሪያ ቤቶች ውስጥ እነዚያን ሁሉ ዓመታት ቢያሳልፉም የሚሰበሩ አልሆኑም፡፡ ባይሆን በቆይታቸው የሒብሩ ቋንቋ አጥንተዋል፡፡ ያሕያ ባይሰበሩም የእስራኤል ባለሥልጣናት ግን በእስር ብቻ ሳይረኩ፤ ከሦስት ዓመት በፊት የግድ ሙከራ አድርገውባቸዋል፡፡ የእስራኤል ባለሥልጣናት በያሕያ ላይ ግድያ ሙከራውን በሚያደርጉበት ወቅት፤ ያሕያ በጋዛ ሆነው ሐማስን እንዲመሩ የተመረጡበት ጊዜ ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲ ትምሕርት በሥነ ጽሑፍ የተመረቁት ያሕያ አስ-ሲንዋር፤ በእስር ቤት በነበሩበት ጊዜ የጻፉት አንድ መጽሐፍ በጠባቂዎች ተወስዶባቸዋል፡፡ “The Thorn and the Carnation” (እሾህ እና አሜከላ እንደማለት) የሚል ርእስ ያለውን የመጽሐፉን ቅጂ ያገኘው የአሜሪካው ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ፤ በኦንላይን ላይብረሪ ውስጥ አስቀምጦት ይገኛል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ጋዛ ውስጥ የሚኖሩት ያሕያ አስ-ሲስዋር፤ በፍልስጤም የነጻነት ትግል ውስጥ ከቤተሰባቸው ብቸኛው ሰው አይደሉም፡፡ ታናሽ ወንድማቸው ሙሐመድ ሲንዋርም እንዲሁ በሐማስ ውስጥ ከፍተኛ አመራር ናቸው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular