Homeዜናና ወቅታዊዜናምክር ቤቱ ሥራ አስኪያጁ በኃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ ውሳኔ ማሳለፉን አሳወቀ

ምክር ቤቱ ሥራ አስኪያጁ በኃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ ውሳኔ ማሳለፉን አሳወቀ

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ አቶ ሪያድ ጀማል ወደ ቀድሞ የሥራ ኃላፊነታቸው እንዲመለሱ ውሳኔ ማሳለፉን በጻፈው ደብዳቤ አሳወቀ፡፡ ምክር ቤቱ ከሐምሌ አጋማሽ አንስቶ ለአቶ ሪያድ ጀማል ሰጠቶ የነበረውን አዲስ ሹመት መሻሩንም አያይዞ ገልጿል፡፡

ምክር ቤቱ አቶ ሪያድ ጀማል በቀድሞ የሥራ አስኪያጅነት ኃላፊነት እንዲቀጥሉ ውሳኔ ማሳለፉን ያስታወቀው፤ ቅዳሜ ሐምሌ 27/2016 በፕሬዝዳንቱ በተጻፈ ደብዳቤ ነው፡፡ ፕሬዝዳንቱ ሐጅ ሡልጣን አማን በፈረሙበት ደብዳቤ፤ አቶ ሪያድ ጀማል ከሐምሌ 16/2016 አንስቶ የምክር ቤቱ የፕሮጀክት እና ኢኮኖሚ ልማት ዳይሬክተር ተደርገው ቢሾሙም፤ በዚያው እለት የመልስ ደብዳቤ መጻፋቸውን ያትታል፡፡

የፕሬዝዳንቱ ደብዳቤ፤ አቶ ሪያድ በእለቱ በጻፉት ደብዳቤ ለሐጅ ሥነ ሥርዐት ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ በተጓዙበት ወቅት፤ “መዋቅሩን ያፋለሰ ተግባር ተፈጽሟል” የሚል ጥያቄ አንስተው፤ ከማንኛውም ኃላፊነት ራሳቸውን ማንሳታቸውን ይገልጻል፡፡ ሆኖም በደብዳቤው ተፈጽሟል የተባለውን ተግባር አልተዘረዘረም፡፡

በምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሐጅ ሡልጣን አማን ደብዳቤ የተጠቀሰውና ሚንበር ቲቪ በተመለከተው አቶ ሪያድ ጀማል ባስገቡት “የሥራ መልቀቂያን የሚመለከት” ደብዳቤ፤ ይኸው ጉዳይ የተጠቀሰበት ቢሆንም፤ ጁመዓ ሐምሌ 26/2016 ስለ ደብዳቤው ይዘት ሥራ አስኪያጁ በሚንበር ቲቪ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ትክክለኛ አይደለም” ሲሉ መልሰዋል፡፡ አቶ ሪያድ በዚሁ ወቅት በሥራ ገበታቸው ላይ እንደሚገኙ ተናግረው ነበር፡፡

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት፤ አቶ ሪያድ ወደ ሥራ አስኪያጅነት ኃላፊነት መመለሳቸውን የሚገልጸው ደብዳቤ የተጻፈውም በማግሥቱ ቅዳሜ ነው፡፡ በፕሬዝዳንቱ ደብዳቤ ላይ፤ አቶ ሪያድ ወደ ሥራቸው የተመለሱት “በተናጠል የወሰዱት ርምጃ” አግባብ ያልነበረ መሆኑን በመገንዘብ “በቃል የጠየቁትን ይቅርታ መሠረት በማድረግ” መሆኑም ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሥራ አስኪያጅነት ይቀጥላሉ የተባሉት አቶ ሪያድ ጀማል፤ ወደ ከተማው ምክር ቤት ኃላፊነት የመጡት በሐምሌ 2014 ነበር፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular