ባለፈው ሳምንት አጋማሽ መሪው እስማኢል ሐኒያህ የተገደሉበት የፍልስጤሙ ሐማስ፤ ከእስራኤል ጋር የሚያደርገውን የተኩስ አቁም ድርድር ለጊዜው ማቆሙ ተነገረ፡፡ እስማኢል ሐኒያህን ለመተካት እየተከናወነ የሚገኘው ሹራ በቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡
ሐማስ ከእስራኤል ጋር የሚያደርገውን የተኩስ አቁም ድርድር ለጊዜው ማቆሙን፤ መቀመጫውን ለንደን ያደረገው “አሸርቅ አል አውሰጥ” ጋዜጣ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ እንደ ጋዜጣው ከሆነ ሐማስ ድርድሩ እንዲቆም ውሳኔ ያሳለፈው፤ የአዲሱን መሪውን ማንነት ይፋ እስከሚያደርግ ድረስ ነው፡፡
ሐማስ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ያደረጋቸው የመሪ ምርጫዎችን በተሳካ መንገድ የማከናወን ልማድ እንዳለው ይነገራል፡፡ የእስማኢል ሐኒያህ ተተኪም በቀጣይ ቀናት ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሐማስን አዲስ መሪ ለመምረጥ የሚካሄደው ሹራ እየተከናወነ የሚገኘው በኳታር ዶሐ ነው።
ሐማስ ድርድሩን ማቆሙ በተነገረበት በዚህ ሰዓት፤ እስራኤል ተደራዳሪዎችን ለመላክ መዘጋጀቷን አስታውቃለች፡፡ ሆኖም የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ሳሚ አቡ ዙህሪ፤ የእስራኤሉ ኔታንያሁ እንዲህ ዐይነት መግለጫ የሚሰጠው የሚፈጽማቸውን ወንጀሎች ለመደበቅ ነው ብለዋል፡፡
ሐማስ እና እስራኤል የሚያደርጉትን የተኩስ አቁም ድርድር የሚያደራድሩት ግብጽ፣ ኳታር እና አሜሪካ ናቸው፡፡ የሦስቱ ሀገራት ተወካዮች ለመጨረሻ ጊዜ በጣሊያን ሮም ከተማ የተገናኙነት ከአንድ ሳምንት በፊት ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ ባለበት የሐማስ መሪ እስማኢል ሐኒያህ ባሳለፍነው ሳምንት ላይ አጋማሽ በኢራን ቴህራን ከተማ ባረፉበት መኖሪያ ቤት ውስጥ እንዳሉ መገደላቸው ይታወሳል። ሐማስ እና የኢራን መንግሥት ለግድያው እስራኤልን ተጠያቂ አድርገዋል። ሐኒያህ ኢራን ውስጥ ለፕሬዝዳንትዋ በዓለ ሲመት አምርተው መገደላቸውን ተከትሎ በቀጣናው ውጥረት ሰፍኗል፡፡
በግዛቷ ሐኒያህ የተገደሉባት ኢራን፣ ለሦስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን በማወጅ የሐማስን መሪ ግብዐተ መሬታቸው ወደተፈፀመበት ኳታር በክብር እንዲሸኙ አድርጋለች። የሐኒያህን ግብዐተ መሬት ተከትሎ በዶሐ እየተከናወነ በሚገኘው ሹራ፣ ሦስት የሐማስ ከፍተኛ አመራሮች ሐኒያህን ሊተኩ ይችላሉ በሚል ግምት እንደተሰጣቸው የኳታር መገናኛ ብዙኃን ጽፈዋል።
ሐኒያህን ሊተኩ ይችላሉ በሚል ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ምክትል ኃላፊው ኸሊል አል ሐያ፣ የቀድሞው የፖለቲካ ኃላፊ ኻሊድ ማሻል እና ሙሣ አቡ መርዙቅ ናቸው።
እስማኢል ሐኒያህ የሐማስ መሪ ሆነው ያገለገሉት እ.አ.አ ከ2017 አንስቶ ነው። (ሚንበር ቲቪ)












