Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችኦሎምፒክን በሒጃብ የሚያደምቁት

ኦሎምፒክን በሒጃብ የሚያደምቁት

ፈረንሳይ ባለፈው ሳምንት ጁመዓ የ2024ቱን ኦሎምፒክ መክፈቻ ለዓለም አቅርባለች፡፡ በዚህ መክፈቻ ሥነ ሥርዐት በነውር “ለመድመቅ” የለፋችው ሀገሪቱ፤ ቀደም ባሉት ሳምንታት ሥሟ ሲነሳ የነበረው ሒጃብ ከምትለብሰዋ አትሌቷ ጋር በገባችበት ንትርክ ነበር፡፡ ፈረንሳይ በ400 ሜትር ዱላ ቅብብል ተወዳዳሪዋ ሲይላ ሱንካምፓ ሒጃብ እንደለበሰች በመክፈቻ ውድድር ላይ መሳተፍ አትችልም ማለቷ ነቀፌታ እንዲሰነዘርባት አድርጓል፡፡ ነቀፌታው በሙስሊሞች ብቻ የተሰነዘረ አልነበረም፡፡ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች እንዲሁም እንደ ሩስያ ያሉ ሀገራትም ውሳኔንም ተችተውታል፡፡ ሀገሪቱ ሒጃብ የምትለብሰዋን ሲይላ ሱንካምፓን ስትገፋ፤ ከሌሎች ሀገራት ተወክለው ኦሎምፒኩን በሒጃብ የሚያደምቁ አትሌቶች ፓሪስ ደርሰዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አምስቱን ተዋወቋቸው፡፡

ቲና ራሒሚ – አውስትራሊያ

ቲና ራሒሚ አውስትራሊያዊት ናት፡፡ በኦሎምፒክ ሀገሯን የምትወክለው በቦክስ ውድድር ነው፡፡ በዚህም የመጀመርያ ሙስሊም ቦክሰኛ ሆናለች፡፡ ራሒሚ እ.አ.አ በ2022 በርሚንግሃም በተካሄደው የኮመን ዌልዝ ውድድር ለሀገሯ ያስገኘችው የነሐስ ሜዳሊያ፤ በፓሪስ ኦሎምፒክ ለወርቅ እንድትጠበቅ አድርጓታል፡፡

ከሰሞኑ ፈረንሳይ የዱላ ቅብብል አትሌቷን በሒጃብ ምክንያት በመክፈቻው አትሳተፍም ማለቷን በአደባባይ ትችት የሰነዘረችበት ራሒሚ፤ ሒጃብ ማድረግን በኩራት አወድሳ በመናገር ትታወቃለች፡፡ ራሒሚ ይህን የምትናገረው ሒጃብ በማድረጓ ምክንያት ጫና ያሳደሩባት ሳይኖሩ ቀርተው እንዳልሆነ ትገልጻለች፡፡ ለራሒሚ በአደባባይ ሒጃብ አድርጋ ለመዝለቋ ስንቅ የሆናት ከሙስሊም ማኅበረሰብ የሚደርላት ድጋፍ ነው፡፡ ራሒሚ በየካቲት ወር ከሀገሯ መገናኛ ብዙኃን ጋር በነበራት ቆይታ፤ ሁሉም ነገር በአላህ እጅ መሆኑን በመናገር፤ ከውድድር በፊት አላህ ከእርሷ ጋር እንዲሆን ዘለግ ያለ የዱዓ ሰዓት ማሳለፍ ዘወትር የምትፈጽመው መሆኑን አስረድታለች፡፡

ሳፊያ አል ሳዪግ – የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች

በኦሎምፒክ ውድድር የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶችን የምትወክለው ሳፊያ፤ ዕድሜዋ 22 ብቻ ነው፡፡ ሳፊያ በኦሎምፒክ ውድድር የምትሳተፈው በብስክሌት ተወዳዳሪነት ነው፡፡ የሳፊያ የስፖርት ፍቅር የጀመረው አባቷ በገዙላት ትንሽዬ ብስክሌት በአቅራቢያዋ ባሉ ሠፈሮች ስትጋልብ ነው፡፡ ይህ የሆነው ከስምንት ዓመት በፊት በ14 ዓመት ዕድሜዋ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የእስያ ጨዋታዎች በብስክሌት ስትሳተፍ፤ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ውድድሯ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በሒጃብ የምተደምቀው ሳፊያ፤ ባለፈው ዓመት ያስመዘገበችው ውጤት በኦሎምፒክ ሜዳሊያ ታገኝለች የሚል ተስፋ እንዲጣልባት አድርጓል፡፡

ዱንያ አቡጣሊብ – ሳዑዲ ዐረቢያ

ዱንያ አቡጣሊብ የቴክዋንዶ ተወዳዳሪ ናት፡፡ የሳዑዲ ዐረቢያ ዜግነት ያላት ዱንያ፤ ቴክዋንዶ መሠልጠን የጀመረችው በስንት ዓመት ዕድሜዋ ነው፡፡ ዱንያ አሁን 27 ዓመት እድሜዋ ላይ ስትደርስ፤ በአሎምፒክ ውድድር ሀገሯን ወክላ ተሳትፋለች፡፡ ይህም በኦሎምፒክ ውድድር ሳዑዲ ዐረቢያን የወከለች የመጀመሪያዋ ሴት ያደርጋታል፡፡

ዱንያ አቡጣሊብ በ2022 በሜክሲኮ እንዲሁም በእስያ ሻምፒዮና ያገኘቻቸው የነሐስ ሜዳሊያዎች በኦሎምፒክ በ49 ኪሎ ግራም ለሜዳሊያ እንድትጠበቅ አድርጓታል፡፡ በኦሎምፒክ ውድድር በቴክዋንዶ የወከለች ቀዳሚዋ ሴት መሆኗ ፈታኝ መሆኑን የምታነገረው ዱንያ፤ ድል ካደረገች የምትጠራው እርሷ ብቻ ሳትሆን ሳዑዲ ዐረቢያም ጭምር በመሆኗ ለዚህ እንደምለፋ ተናግራለች፡፡

መርዋ ባውዛኒ – ቱኒዝያ

የምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳሪዋ መርዋ ባውዛኒ፤ በሒጃብ ኦሎምፒክን ከሚያደምቁ አትሌቶች መካከል ትጠቀሳለች፡፡ አትሌቷ በፓሪስ የምታደርገው ተሳትፎ፤ በኦሎምፒክ ለሁለተኛ ጊዜ የምታደርገው ነው፡፡ መርዋ በ2020 በቶክዮ ስድስተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች፡፡ በዚህ ዓመት የኦሎምፒክ ተሳትፎ ይህን ደረጃ ለማሻሻል እንደምትሮጥ ይጠበቃል፡፡ መርዋ በኦሎምፒክም ሆነ በሌሎች ውድድሮች ተሳትፎዋ በሒጃብ ደምቃ መታየትዋን እንደምትወደው ደጋግማ ትናገራለች፡፡ መርዋ ይህን ስታደርግ ለሙስሊም ሴቶች አርኣያ ለመሆን ነው ትላለች፡፡ ቱኒዝያዊቷ አትሌት ሙስሊም ሴቶች የሃይማኖታቸውን እሴቶች አስጠብቀው ሀገራቸውን በትላልቅ መድረኮች መወከል ይችላሉ የሚለውንም ጭምር ማሳየት ፍላጎቷ መሆኑን ትገልጻለች፡፡

ኸዲጃ ኤል ማርዲ – ሞሮኮ

ኸዲዳ ሞሮኮን በኦሎምፒክ የምትወክለው በቦክስ ውድድር ነው፡፡ በልጅነት የቦክስ ውድድር ፍቅር ጸንቶባት፤ በድብቅ ልምምድ ታደርግ ነበር፡፡ ወደ ፕሮፌሽናል ውድድር መድረክ የመጣችው ኸዲጃ፤ ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፍ የአማተሮች ውድድር ባደረገችው ውድድር ያገኘችው የወርቅ ሜዳሊያ ቀዳሚዋ ዐረብ እና አፍሪካዊ ሴት ተወዳዳሪ እንድትሆን አስችሏታል፡፡ ኸዲጃ፤ አትሌቶቿ ሒጃብ እንዳያደርጉ ስትታገል በቆየችው ፈረንሳይ እየተካሔደ በሚገኘው የፓሪስ ኦሎምፒክ ሞሮኮን ስትወክል በሒጃብ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

 

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular