Homeዜናና ወቅታዊዜናእስማኢል ሐኒያህ ማን ናቸው?

እስማኢል ሐኒያህ ማን ናቸው?

“በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩሕሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፤ እነዚያን በአላህ መንገድ የተገደሉትን ሙታን አድርገህ አትገምታቸው፡፡ በርግጥ እነርሱ እጌታቸው ዘንድ ሕያዋን ናቸው፤ ሲሳይን የሚቀበሉ ናቸው፡፡”

ይህን የቁርኣን አንቀጽ የተጠቀመው የፍልስጤሙ ሐማስ ነው፡፡ ሐማስ መሪው እስማኢል ሐኒያህ፤ ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 24/2016 ማለዳ ሰማዕት ሆነዋል ሲል አስታውቋል፡፡ እንደ መረጃዎች ከሆነ ሐኒያህ ግድያ የተፈጸማቸው በኢራን መዲና ቴህራን ነው፡፡ ጥቃቱን የተሰነዘረው በፅዮናዊያን መሆኑን የገለጸው ሐማስ፤ ጥቃቱን ግብዝነት “የተሞላበት ነው” ሲል ኮንኖታል። እስማኢል ሐኒያህ የተገደሉት በቴህራን ከተማ በአዲሱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳት በዓለ ሲመት ላይ ከታደሙ በኋላ ነው፡፡ ሐኒያህ በአፈሯ የተገደሉባት ኢራን በበኩሏ፤ የሐማስ መሪ የተገደሉት በአንድ ጥበቃቸው አማካኝት ነው ብላለች፡፡ ይህ መረጃ በሦስተኛ ወገን አልተረጋገጠም፡፡

ለመሆኑ በድርጅታቸው ሐማስ በፅዮናዊያን መገደላቸው የተነገረው እስማኢል ሐኒያህ ማን ናቸው?

እስማኢል ዐብዱሰላም አሕመድ ሐኒያህ የተወለደው እ.አ.አ በግንቦት 1963 በአልሻይቲ የስተኞች መጠለያ ውስጥ ነው፡፡ የሐኒያህ ቤተሰብ በወቅቱ በጋዛ ሰርጥ ውስጥ በሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለመኖር የተገደደው፤ ከመኖሪያው አሽኬሎን አካባቢው በግዳጅ በመፈናቀሉ ነበር፡፡

በስደተኛ ጣቢያ ውስጥ የተወለደው ሐኒያህ፤ ገና በለጋ እድሜያው ቤተሰቡን ለመደገፍ በሥራ ላይ ተሰማርቷል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባቋቋማቸው ትምህርት ቤቶች የተማረው ታዳጊው ሐኒያህ፤ የከፍተኛ ትምህርቱን በኢስላሚክ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ጋዛ ተከታትሏል፡፡ እስማኤል ሐኒያህ የመጀመርያ ዲግሪውን ያገኘው በእስላማዊ ሥነ ጽሑፍ ነው፡፡

ሐኒያህ በትምህርት ቤት ውስጥ ባለበት በፍልስጤም የትግል እንቅስቃሴዎች መሳተፍ መጀመሩ ይነገራል፡፡ በዚህም ሐኒያህ እስራኤልን ተቃውመው በሚደረጉ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በሠፊው ተሳትፎ ያደርግ እንደነበረም ሕይወት ታሪኩ ያሳያል፡፡ በእነዚህ የትግል እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሲሳተፍ በእስራኤል ወታደራዊ እስር ቤቶች የተለያዩ እንግልቶች ተፈጽመውበታል፡፡

ወጣቱ እስማኢል ሐኒያህ የትግል ተሳትፎው እያደገ መጥቶ ሐማስን በመቀላቀል በተለያዩ የአመራር እርከኖች ላይ ተሳትፎ ሲያደርግ የቆየ ነው፡፡ እስማኢል ሐኒያህ በሐማስ የመሪነት እንቅስቃሴው የበታች አመራር ሆኖ እያገለገለ በነበረበት በ2003 አንድ አጥፍቶ ጠፊ ባፈነዳው ቦምብ መጠነኛ ጉዳት አስተናግዷል፡፡

ሐኒያህ በትግል ውስጥ ባካበተው ልምድ ወደ ከፍተኛ ሥልጣን እርከን የተሸጋገረው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ በጋዛ የሐማስ መንፈሣዊ መሪ የሸይኽ አሕመድ ያሲን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው እንዲሠሩ የተደረጉት ሐኒያህ፤ በ2006 የፍልስጤም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል።

ከዚህ ሹመት በኋላ የፍልስጤምን ምድር በኃይል የወረረችው እስራኤል፤ በፍልስጤም አስተዳደር ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን በመጣል ሐማስን ለማንበርከክ ሙከራዋን የቀጠለች ቢሆንም፤ ሐኒያህ ግን የሀገርነት እውቅና በመንፈግ ሐማስ እየተጠናከረ እንደሚሄድ በተደጋጋሚ ይናገሩ ነበር፡፡

አስረኛው የፍልስጤም ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት እስማኢል ሐኒያህ፤ በጋዛ በተፈጠሩ ፖለቲካዊ ለውጦች ምክንያት በ2016 ጋዛን በመልቀቅ መኖሪያቸውን ኳታር ለማድረግ ተገደዋል፡፡

እስማኢል ሐኒያህ ቋሚ መኖሪያቸውን ካደረጉባት የኳታሯ ዶሐ፤ በተደጋጋሚ የሚያቀኑት ወደ ቱርክ ኢስታምቡል ነበር፡፡ እስራኤል በመስከረም ወር መጨረሻ በጋዛ በንጹሐን ላይ በሰነዘረችው የቦምብ ጥቃት ሺሕዎች ሲገደሉ፤ ግድያውን በቴሌቪዥን ያወገዙትም ኢስታምቡል ውስጥ ባሉበት ነበር፡፡ ሐኒያህ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት እስራኤል በጋዛ ላይ የከፈተችውን ጦርነት ካላቆመች ሐማስ በምርኮ ያዛቸውን ሠፋሪዎች እንደማይለቅ ተናግረው ነበር፡፡

እስማኢል ሐኒያህ እና ሬሲብ ጠይብ ኤርዶጋን

የእስማኢል ሐኒያህ ግድያ ከተሰማ በኋላ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡ ግድያው የተፈጸመበት የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ናስር ከናኒ፤ የሐኒያህ ሰማዕት መሆን በቴህራን እና ፍልስጤም መካከል ያለውን ጥልቅ እና የማይበጠስ ትስስር ያጠናክራል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ሐኒያህ ለበርካታ ጊዜያት ይመላለሱባት የነበረችው ቱርክ፤ ግድያው እስራኤል ለሰላም ፍላጎት እንደሌላት በድጋሚ ያሳየችበት ነው ብላለች፡፡ ግድያውን ሩስያ፣ ማሌዥያ እና ኳታርም አውግዘውታል፡፡ ሩስያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ባወጣችው መግለጫ፤ በፍጹም ተቀባይነት የለውም ያለችው ግድያ፤ የቀጣናውን ውጥረት የሚጨምር እንዳይሆንም ስጋቷን ገልጻለች፡፡  

የሐማሱ መሪ እስማኢል ሐኒያህ ከትግል ሕይወታቸው ውጪ ቤተሰብ መሥርተው 13 ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ዛሬ ማለዳ መገደላቸው ይፋ የተደረገው እስማኢል ሐኒያህ፤ የአብራካቸው ክፋይ ከሆኑ ልጆቻቸው ውስጥ ሦስቱ በቅርቡ በእስራኤል ጥቃት ተገድለውባቸዋል፡፡ ከልጆቻቸው በተጨማሪም አራት የልጅ ልጆቻቸው በእስራኤል ጥቃት ሕይወታቸው ተነጥቋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular