የፍልስጤሙ ሐማስ ትናንት ረቡዕ የተገደሉት መሪው እስማኢል ሐኒያህ የቀብር ሥነ ሥርዐት፤ ነገ ጁመዓ እንደሚፈጸም አስታወቀ፡፡ የሐማስ መሪ ቀብር የሚከናወነው ለዓመታት መኖሪያቸው በነበረችው ዶሐ እንደሚሆንም ቡድኑ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡
ሐማስ በመግለጫው፤ የእስማኢል ሐኒያህ ግብዐተ መሬት በኳታር ከመፈጸሙ አስቀድሞ ግድያው በተፈጸመባቸው የኢራን መዲና ቴሕራን የሽኝት ሥነ ሥርዐት እንደሚካሔድ ገልጿል፡፡ እንደ ሐማስ ከሆነ የሐኒያህ አስከሬን በነገው እለት ቀደም ብሎ ወደ ኳታር ይጓጓዛል፡፡ በዶሐ በሚፈጸመው የቀብር ሥነ ሥርዐት ላይ የዐረብ ሀገራት መሪዎች እና የእስልምና ሊቃውንት የሚታደሙት ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም ሐማስ ጠቁሟል፡፡
የሐኒያህ ሽኝት የሚደረግባት አራን፤ ሥነ ሥርዐቱን ያስጀመረችው በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴሕራን ውስጥ መሆኑን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
የእስማኢል ሐኒያህ ግድያ የተፈጸመው በፅዮናዊያን መሆኑን ሐማስም ሆነ ኢራን ገልጸዋል፡፡ በግዛቷ ሐኒያህ የተገደሉባት ኢራን፤ የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን አውጃለች፡፡ ኢራን በተጨማሪም ለግድያው አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት ጊዜ እና ሁኔታዎችን እንደምትጠብቅ በባለሥልጣናቷ በኩል አሳውቃለች፡፡
ከሐኒያህ ግድያ በኋላ በጋዛ እና ዌስት ባንክ ከባድ የሐዘን ድባብ እንደሚስተዋል አልጀዚራ ከሥፍው ያወጣው ዘገባ ያመለክታል፡፡ በሥፍራዎቹ የሚገኙ ፍልስጤማዊያን የትግል መሪያቸውን መገደል ተከትሎ ሐዘን እና ቁጣቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጹ ታይተዋል፡፡
አልጀዚራ ያናገራቸው ማዕከላዊ ጋዛ ውስጥ በሚገኘው በዴር አል በላህ የተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ የሚኖሩት 67 እድሜ ያላቸው ሳልህ አል ሻናት የተባሉ ፍልስጤማዊ፤ “እስማኢል ሐኒያህ የሐማስ ብቻ ሳይሆን የፍልስጤም መሪ ነበሩ፡፡ እርሳቸውን ማጣት ኪሳራው ከፍተኛ ነው” ብለዋል፡፡
በመጠለያው ውስጥ ለጣቢያው የተናገረችው ዛህዋ አል ሳሙኒ በበኩሏ፤ ሐኒያህ ጋዛን በመልቀቅ ወደ ዶሐ ከማቅናታቸው በፊት እንደምታውቃቸው በመግለጽ፤ “እንደ መሪ ሳይሆን ለእኛ ቅርብ ሰው ነበሩ” ስትል ወቅቱን አስታውሳለች፡፡ ሐኒያህ በደስታም ሆነ በሐዘን አብረዋቸው እንዳሳለፉም አክላለች፡፡ በመጠለያው የሚገኙት ሌሎች ፍልስጤዊያንም እንባቸውን እየዘሩ ፍልስጤም ትልቅ መሪ ማጣቷን ለቴሌቪዥን ጣቢያው ተናግረዋል፡፡
እስማኢል ዐብዱሰላም አሕመድ ሐኒያህ የተወለዱት እ.አ.አ በግንቦት 1963 በአልሻይቲ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ነበር፡፡ ሐኒያህ ቤተሰብ መሥርተው 13 ልጆችን አፍርተዋል፡፡ እስማአል ሐኒያህ የፍልስጤም አስረኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ለጥቂት ጊዜያት አገልግለዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












