የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም፤ ሜታ ኩባንያ የሐማሱ መሪ እስማኢል ሐኒያህን አስመልክቶ ያስተላለፉትን የሐዘን መልዕክት በመሰረዙ ብርቱ ትችት ሰንዝረዋል፡፡ ሜታ ኩባንያ ትናንት ረቡዕ እስማኢል ሐኒያህን የተመለከቱ ፖስቶችን ሲያስወግድ ውሏል፡፡
አንዋር ኢብራሂም ትናንት የሐማሱ መሪ እስማኢል ሐኒያህ ግድያ ከተሰማ በኋላ፤ ለሌላ የድርጅቱ አመራር ደውለው የሐዘን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ይህንኑ የስልክ ልውውጥ ሜታ በሚያስተዳድረው ፌስቡክ ገጽ ላይ ለጥፈውታል፡፡
ሆኖም ከጥቂት ቆይታ በኋላ ሜታ ኩባንያ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሐዘን መልእክት ከፌስቡክ ላይ አስወግዶታል፡፡ በዚህ የሜታ ድርጊት የተበሳጩት ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም፤ ድርጊቱን ተችተው በዚያው በፌስቡክ ጽፈዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሜታ እንዲደርስ በማለት ባስተላለፉት ይፋዊ መልዕክት፤ ድርጊቱን “ድፍረት” ነው ሲሉ የገለጹት ሲሆን ኩባንያውም “የጨቋኙ የእስራኤል ጽዮናዊ አገዛዝ መጠቀሚያ ከመሆን” እንዲታቀብም አሳስበዋል፡፡ አንዋር ኢብራሂም ትችት የተሰነዘረበት ሜታ፤ እስካሁን ድረስ ምላሽ አልሰጠም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም በሚመሯት ማሌዥያ፤ ከነዋሪው ውስጥ 63 በመቶው ሙስሊም ነው፡፡ ማሌዥያ የፍልስጤማዊያንን ትግል እንደምትደግፍም በተደጋጋሚ ገልጻለች፡፡ የሐዘን መልዕክታቸው በሜታ ኩባንያ የተሰረዘባቸው የማሌዥያው ጠቅላይ ሚኒስትር፤ በግንቦት ወር ከእስማኢል ሐኒያህ ጋር በኳታር ዶሐ ተገናኝተው ነበር፡፡ አንዋር ኢብራሂም ከሐኒያህ ሐማስ ጋር ግንኙነታቸው መልካም መሆኑንም ይናገራሉ፡፡
አንዋር ኢብራሂም እና እስማኢል በኳታር በተገናኙበት ወቅት በተመሳሳይ ሜታ ኩባንያ የሁለቱን ሰዎች በአካል መገናኘት ሽፋን የተሰጠበትን የማሌዥያ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ሠርዞት ነበር፡፡

ከሐማሱ መሪ ግድያ በኋላ የማሌዥያውን ጠቅላይ ሚኒስትር የሐዘን መልዕክት በመሰረዙ ነቀፌታ ያስተናገደው ሜታ ኩባንያ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተመሳሳይ ስለ እስማኢል ሐኒያህ የሚጻፉ መልዕክቶችን ሲሰርዝ በመዋሉ በበርካታ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚዎች ቅሬታ ሲቀርብበት ነበር፡፡
በድርጊቱ ቅሬታ የቀረበበት ሜታ፤ የፍልስጤሙን ሐማስ “አደገኛ” በሚል ፈርጅ ካስቀመጣቸው ድርጅቶች ውስጥ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ሜታ ኩባንያ፤ ፌስቡክ፣ ዋትሳፕ እና ኢንስታግራምን በሥሩ የሚያስተዳድር ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












