የቱርኪዬ መንግሥት የሐማሱ መሪ እስማኢል ሐኒያህን የተመለከቱ ይዘቶችን ይሠርዛል ያለውን ኢንስታግራምን እንዳይታይ ማገዱን አስታወቀ፡፡ ኢንስታግራምን የሚያስተዳድረው ሜታ በአንድ ሳምንት ከሁለት መንግሥታት ቅሬታ ቀርቦበታል፡፡
ቱርኪዬ በሜታ ኩባንያ ስር የሚተዳደረውን ኢንስታግራምን እንዳይታይ መገዷን ያስታወቀችው፤ የፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን ጽሕፈት ቤት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት ፋህረቲን አልቱን፤ መተግበሪያው የሐማሱ መሪ እስማኢል ሐኒያን ግድያን የተመለከቱ የሐዘን መልእክቶችን እየሠረዘ ነው ካሉ በኋላ ነው፡፡
ማኅበራዊ ትስስር ገጹ የፈጸመውን ተግባር “ሳንሱር ነው” ያሉት የኮሙኒኬሽን ኃላፊው፤ በቀጣይም በተመሳሳይ ሐሳብን ለመግለጽ ነጻነት ዘብ እንደሚቆሙ ገልጸዋል፡፡ የቱርኪዬ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን በኢንስታግራም ላይ የጣለው እገዳ ዜና የመጣውም ከዚህ በኋላ ነው፡፡
በቱርኪዬ የእገዳ ውሳኔ የተላለፈበት ኢንስታግራምን የሚያስተዳድረው ሜታ ኩባንያ፤ ከሁለት ቀናት በፊት በቴህራን የተፈጸመውን የሐማሱን መሪ እስማኢል ሐኒያህን ግድያ ተከትሎ፤ የሐዘን መልዕክቶችን ይሠርዛል በሚል ከመንግሥታት ቅሬታ ሲቀርብበት ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
ትናንት ሐሙስ የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም፤ ሜታ ኩባንያ የሐማሱ መሪ እስማኢል ሐኒያህን አስመልክቶ ያስተላለፉትን የሐዘን መልዕክት በመሠረዙ ብርቱ ትችት ሰንዝረውበት ነበር፡፡ ሜታ ኩባንያ ረቡዕ እስማኢል ሐኒያህን የተመለከቱ ይዘቶችን ኢትዮጵያን ጨምሮ ሲሠርዝ መዋሉን ተጠቃሚዎች ሲገልጹ ተስተውለዋል፡፡
የኩባንያውን ድርጊት ተከትሎ ኢስትግራምን ያገደችው ቱርኪዬ፤ በፕሬዝዳንቷ ጽሕፈት ቤት ኮሙኒኬሽን ኃላፊው ፋህረቲን አልቱን በኩል፤ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ “ከፍልስጤም ወንድሞቻችን ጎን መቆማችንን እናሳያለን” ብላለች፡፡
ረቡዕ ማለዳ ኅልፈታቸው የተሰማው የሐማሱ መሪ እስማኢል ሐኒያህ፤ ከቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን ጋር ጥብቅ ወዳጅነት እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ ያለፉትን ዓመታት በኳታር ዶሓ ስደት ላይ የቆዩት የሐማስ መሪ፤ በተደጋጋሚ ከሚመላለሱባቸው ጥቂት ሀገራት መካከል ቱርኪዬ ከፊት ትቀመጣለች፡፡
የሐኒያህን የሐዘን መልዕክት በመሠረዝ በቱርኪዬ መንግሥት እገዳ የተጣለበት በሜታ ኩባንያ ስር የሚተዳደረው ኢንስታግራም፤ በሀገሪቱ 50 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች እንዳሉት የቱርኪዬ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ያመለክታል፡፡ ሜታ ኩባንያ፤ አንስታግራምን ጨምሮ፣ ዋትሳፕ እና ፌስቡክን በሥሩ እንደሚያስተዳድር ይታወቃል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)