Homeዜናና ወቅታዊዜናብር ከዶላር ጋር የነበረው የምንዛሬ ምጣኔ በ30 በመቶ ተዳከመ

ብር ከዶላር ጋር የነበረው የምንዛሬ ምጣኔ በ30 በመቶ ተዳከመ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ተመን በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወሰንበት የገበያ ሥርዐት እንደተሸጋገረ ማስታወቁን ተከትሎ፤ ብር ከዶላር ጋር የነበረው የምንዛሬ ምጣኔ በ30 በመቶ ተዳከመ፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በባንኮች በ56.6 ይሸጥ የነበረው አንድ የአሜሪካን ዶላር፤ ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 22/2016 76.2 ገብቷል፡፡

ይህ ውሳኔ ብር ከዶላር አንጻር የነበረውን የምንዛሬ ምጣኔ በ30 በመቶ ያዳከመ ነው፡፡ የምንዛሬ ለውጡ የመጣው የኢትዮጵያ መንግሥት በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሬ ሊተገብር መሆኑን ካስታወቀ በኋላ ነው፡፡ መንግሥት ይህን የገለጸው ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ መግባቷን ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው።

ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ሥርዐት፣ የውጭ ምንዛሬ በገበያው አማካኝነት እንዲበየን የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል። ውሳኔውን ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሬ ተመንን ማረጋገጥ በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሬ መዛባት ለማስተካከል ይረዳል ብለዋል።

መንግሥት የውጭ ምንዛሬ ተመን በባንኮች እና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወሰንበት የገበያ ሥርዐት እንደተሸጋገረ ሲያሳውቅ፤ ሌሎች ማሻሻያዎችም ተከትለዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የውጭ ምንዛሬን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማስተላለፍ ግዴታ እንዲቀር ተደርጓል። በዚህ አሠራር ላኪዎች እና ንግድ ባንኮች ያፈሩትን የውጭ ምንዛሬ ለራሳቸው ማስቀረት እንደሚችሉ ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል በ38 የገቢ ንግድ ሸቀጦች ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ መነሳቱንም ብሔራዊ ባንክ ገልጿል።

ኢትዮጵያ ወደ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ ስትገባ ከዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ድርጅት ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት ከፋይናንስ ተቋማት በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ በርካታ ቢሊዮን ዶላር እንደምታገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular