የብሪክስ አባል ሀገራት የቁርኣን ውድድር ከረቡዕ አንስቶ እስከ ትናንት ጁመዓ ሐምሌ 19/2016 ድረስ በሩስያ ካዛን ከተማ ተካሔዶ ተጠናቋል። በዚህ ውድድር ላይ ከተሳተፉ 22 ሀገራት መካከል ባሕሬን አሸናፊ ሆናለች።
ውድድሩ በባሕሬኑ ሙሐመድ ሰሚር አሸናፊነት ቢጠናቀቅም፣ ሁለተኛ ደረጃ ያገኘው ግብጻዊው ዐብዱልከሪም ካሚል የተለየ ትኩረት ስቧል።
ካዛን ባስተናገደችው የቁርኣን ውድድር፤ ተወዳዳሪዎች በቁርኣን ንባብ ሒደት ፊደላትን ከትክክለኛ ቦታቸው ማውጣትና የሚገባቸውን ባሕሪያት በመስጠት ማንበብ ይጠበቅባቸው ነበር።
ግብጻዊው ተወዳዳሪ ዐብዱልከሪም ግን በቁርኣን እየታገዘ ማንበብ የሚችል አይደለም። ሲወለድ ባጋጠመው መጋረድ በዐይኖቹ መታገዝ አይችልም። ስለዚህ በልቡ ያተመውን ቁርኣን ለውድድሩ ዳኞች ማቅረብ ነበረበት። በዚህ መልኩ ተወዳዳሮ ሁለተኛው አሸናፊ ሆኗል።
የቁርኣን ቲላዋ ውድድሩ የተዘጋጀው፤ በሩስያ የእስልምና ሃይማኖት ጉዳዮች የሥራ አመራር ቦርድ፣ በሙሐመድ ቢን ዛይድ ዩኒቨርሲቲ እና በሩስያዋ ታታርስታን ሪፐብሊክ ነው፡፡
እነዚህ የብሪክስ አባል ሀገራት የቁርኣን ውድድር አዘጋጆች፣ ለግብጻዊው ተወዳዳሪ ትኩረት እንዲሰጡ ያስገደዳቸው ሌላም ጉዳይ አለ። አዘጋጆቹ በርከት ያሉ የውድድሩን ክፍሎች የሀገሬው ሰዎች በነጻ እንዲታደሙ በራቸውን ክፍት ቢያደርጉም፣ መግቢያ ይከፈልባቸው በነበሩ አጋጣሚዎች የተሰበሰበው ገንዘብ ለብሬል ቁርኣን ኅትመት እንዲውል እቅድ ይዘዋል። (ሚንበር ቲቪ)












