የብሪክስ ሀገራት የቁርኣን ቲላዋ ውድድር በባሕሬናዊው ተወዳዳሪ ሙሐመድ ሰሚር ሙሐመድ አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ በሩስያ ታታርስታን ግዛት ዋና መዲና ካዛን ለሦስት ቀናት የተከናወነው ውድድር የተጠናቀቀው ትናንት ጁመዓ ሐምሌ 20/2016 ነው፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሃያ ሀገራት በተሳተፉበት የቁርኣን ቲላዋ ውድድር፤ በባሕሬናዊው ሙሐመድ ሰሚር አሸናፊነት ሲጠናቀቅ፤ በውድድሩ ሁለተኛ ደረጃ ያገኘው ግብጻዊው ዐብዱልከሪም ካሚል አቲያህ ነው፡፡ የኢራኑ ኦሚድ ሑሴኒነጃድ ደግሞ ሦስተኛ ወጥቷል፡፡
በውድድሩ ላይ ከብሪክስ አባል ሀገራት ተወዳዳሪዎች ውጪ ከዐረብ ሀገራት የተወከሉ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ከብሪክስ ሀገራት ውስጥ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የአዘጋጇ ሩስያ፣ ብራዚል፣ ቻይና፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች እና ባንግላዴሽ ዜጎች በውድድሩ ላይ ተገኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያን በመወከል በውድድሩ ላይ የተሳተፈው ዐብዱልወሃብ ሙስጠፋ የተባለ ወጣት ነው፡፡
የውድድሩ አዘጋጅ ካዛን ከተማ፤ ታዳሚያን ውድድሩን እንዲከታታሉ በሮችን በነጻ ክፍት አድርጋ ነበር፡፡ በተጨማሪም በመጨረሻው ቀን በውድድር ሥፍራው የሚገኙ ታዳሚያን ነጻ የቁርኣን ሥጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡
የቁርኣን ቲላዋ ውድድሩ የተዘጋጀው፤ በሩስያ የእስልምና ሃይማኖት ጉዳዮች የሥራ አመራር ቦርድ፣ በሙሐመድ ቢን ዛይድ ዩኒቨርሲቲ እና በሩስያዋ ታታርስታን ሪፐብሊክ ነው፡፡
የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል የሆኑት ሩሻን አቢያሶቭ፤ የቁርኣን ቲላዋ ወድድሩ በየዓመቱ እንደሚቀጥል በመግለጽ፤ ውድድሩን የብሪክስ አባል ሀገራት እየተፈራረቁ እንዲያዘጋጁት እቅድ መኖሩን ቀድመው አሳውቀዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












