የሩስያ መንግሥት የኦሎምፒክ አስተናጋጇ ፈረንሳይ፤ ተወዳዳሪ አትሌቷን በሒጃብ ምክንያት በመክፈቻው ሥነ ሥርዐት ላይ እንዳትገኝ በመከልክሏ ነቀፌታ ሰነዘረች፡፡ ሩስያ ክልከላውን ከኦሎምፒክ መርሆ ያፈነገጠ ነው ብላዋለች፡፡
የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ፤ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ ይህኑ አንጸባርቀዋል፡፡
ሩስያ በፈረንሳይ ላይ የሰነዘረችው ነቀፌታ የመጣው፤ ዛሬ ጁመዓ ሐምሌ 19/2016 ምሽት ላይ በሚጀመረው የ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ የምትሳተፈው ፈረንሳዊቷ አትሌት ሱንካምፓ ሲይላ፤ በሒጃብዋ ምክንያት በሥነ ሥርዐቱ ላይ እንደማትሳተፍ ከተገለጸ በኋላ ነው፡፡
ፈረንሳይ በ400 ሜትር ዱላ ቅብብል ተወዳዳሪዋ ሱንካምፓ ያስተላለፈችውን ውሳኔ፤ እንደ ሩስያ ሁሉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዐይነት ድርጅቶች ትችት ሰንዝረውበታል፡፡ አትሌቷ ሒጃብ በመልበሷ ምክንያት ከኦሎምፒክ መክፈቻ ሥነ ሥርዐት ያስቀረችው ፈረንሳይ፤ ውሳኔን ያሳለፈችው አራምደዋለሁ የምትለውን የሴኩላሪዝም ፖሊሲ ተገን በማድረግ ነው፡፡
የመብቶች ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኦሎምፒክ ውድድር አዘጋጇ ፈረንሳይ፤ ሙስሊም አትሌቶቿ ሒጃብ እንዳያደርጉ መከልከሏን የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው ያለው ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴንም ውሳኔውን በዝምታ በማለፉ ተችቶታል፡፡ የፈረንሳይ ውሳኔ ከመብት ድርጅቶች በተጨማሪ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መግለጫ እንዲያወጣ ያስገደደ ነው፡፡
ዛሬ ጁመዐ በሚከፈተው የኦሎምፒክ ውድድር ላይ ፈረንሳይን የምትወክለው ሱንካምፓ ሲይላ፤ ሀገሯ ሒጃብን በተመለከተ የያዘችውን አቋም በማኅበራዊ ትስስር መድረክ ላይ ነቀፌታ ሰንዝራበታለች፡፡ አትሌቷ በኢንስትታግራም ገጹዋ፤ ሀገሯ በምታዘጋጀው የኦሎምፒክ ውድድር ላይ ለመሳተፍ አትሌቶችን መርጣ በመክፈቻ ሥነ ሥርዐቱ ላይ ሒጃብ በማድረጋቸው እንዳይሳተፉ መከልከሏን ተችታ ጽፋለች፡፡
ፈረንሳይ፤ ሲይላ ሒጃብ አላወልቅም በሚል አቋማ በመጽናቷ፤ በመክፈቻው ሥነ ሥርዐት ላይ መሳተፍ እንድትችል መፍትሔ እፈልጋለሁ ማለቷን የሀገሪቱ ጋዜጦች ቢጽፉም፤ ምን ዐይነት መፍትሔ እንዳቀዱ ግን ግልጽ አላደረጉም፡፡ የፓሪሱ ላፓሪዝያን ጋዜጣ በትናንት እትሙ አትሌቷ ከሒጃብ ውጪ ጸጉሯን ለመሸፈን ባርኔጣ ታደርጋለች ቢልም አትሌቷ እስካሁን በሒጃብ ጸንታለች፡፡
በዛሬው እለት የሚጀመረው የፓሪስ ኦሎምፒክ፤ ለቀጣይ ሁለት ሳምንታት የሚካሄድ ነው፡፡ በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያም በአትሌቲክስ ተሳታፊ ትሆናለች፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












