Homeዜናና ወቅታዊዜናኢትዮጵያን ጨምሮ ሃያ ሀገራት የሚሳተፉበት የቁርኣን ቲላዋ ውድድር በሩስያ እየተካሄደ ነው

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሃያ ሀገራት የሚሳተፉበት የቁርኣን ቲላዋ ውድድር በሩስያ እየተካሄደ ነው

በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ብሪክን የተቀላቀለችውን ኢትዮጵያን ጨምሮ ሃያ ሀገራት የሚሳተፉበት የቁርኣን ቲላዋ ውድድር፤ በሩስያ ካዛን እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በውድድሩ ላይ ከብሪክስ አባል ሀገራት ተወዳዳሪዎች ውጪ ከዐረብ ሀገራት የተወከሉ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ትናንት ረቡዕ ሐምሌ 17/2016 የተጀመረው የቁርኣን ውድድር የተዘጋጀው፤ በሩስያ የእስልምና ሃይማኖት ጉዳዮች የሥራ አመራር ቦርድ፣ በሙሐመድ ቢን ዛይድ ዩኒቨርሲቲ እና በሩስያዋ ታታርስታን ሪፐብሊክ ነው፡፡

በውድድሩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ተወዳዳሪዎች የተመረጡት ቀድመው ለአዘጋጆቹ በላኩት ቪድዮ ላይ ተመርኩዞ መሆኑን የሩስያ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ያመለክታል፡፡ ከኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ዐብዱልወሃብ ሙስጠፋ የተባለ ወጣት ወደ ታታርስታን ግዛት መቀመጫ ካዛን ማምራቱ ታውቋል፡፡

ዐብዱልወሃብ ሙስጠፋ

ለሦስት ቀናት የሚካሄደው ውድድር በዋነኝነት የሚያሳትፈው የብሪክስ አባል ሀገራት ተወዳዳሪዎችን ቢሆንም፣ ከተለያዩ ዐረብ ሀገራት ተወዳዳሪዎች ተገኝተዋል፡፡ ከብሪክስ ሀገራት ውስጥ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የአዘጋጇ ሩስያ፣ ብራዚል፣ ቻይና፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች እና ባንግላዴሽ ዜጎች በውድድሩ ላይ ተገኝተዋል፡፡

የውድድሩ አዘጋጅ ካዛን ከተማ፤ ታዳሚያን ውድድሩን እንዲከታታሉ በሮችን በነጻ ክፍት ማድረጓ ታውቋል፡፡ በተጨማሪም በመጨረሻው ቀን በውድድር ሥፍራው የሚገኙ ታዳሚያን ነጻ የቁርኣን ሥጦታ ይበረከትላቸዋል ተብሏል፡፡

የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል የሆኑት ሩሻን አቢያሶቭ፤ የቁርኣን ቲላዋ ወድድሩ በየዓመቱ እንደሚቀጥል በመግለጽ፤ ውድድሩን የብሪክስ አባል ሀገራት እየተፈራረቁ እንዲያዘጋጁት እቅድ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

በዝግጅቱ ላይ ከቁርኣን ቲላዋ ውድድር በተጨማሪ የተለያዩ የካሊግራፊ ሥራዎች አውደ ርዕይ ለታዳሚያን ክፍት ተደርጓል፡፡

በሩስያ ታታርስታን ግዛት ውስጥ በምትገኘው ካዛን ከተማ እየተከናወነ በሚገኘው የቁርኣን ቲላዋ ውድድር፤ ከተለያዩ ሀገራት የተጋበዙ ሊቃውንት እና የሃይማኖት መሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ከኢትዮጵያም የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ካዛን እንደሚገኙ ምክር ቤቱ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular