Homeየቲቪ ፕሮግራሞችበሁለት ወር ጊዜ ውስጥ አዲስ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ ሊደረግ ነው

በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ አዲስ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ ሊደረግ ነው

በኢትዮጵያ በቀጣይ ሁለት ወራት አዲስ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ ሊደረግ ነው፡፡ በአዲሱ የታሪፍ ማሻሻያ የመኖሪያ ቤት ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች የሚከፍሉት ዋጋ እስከ ሦስት እጥፍ ጭማሪ ሊደረግበት ይችላል ተብሏል፡፡

የታሪፍ ማሻሻያውን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበው የኢትዮጵያ ኢነርጂ እና ነዳጅ ባለሥልጣን፤ ያቀረበው እቅድ ተቀባይነት ማግኘቱ ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሁን በሥራ ላይ ያለውን ታሪፍ በማሻሻል፣ ከወቅቱ የዋጋ ንረት ጋር ሊሄድ የሚችል አዲስ ታሪፍ ለማውጣት ጥናት እያካሄደ መሆኑን ከዚህ ቀደም አስታውቆ ነበር፡፡ በሀገሪቱ አሁን በሥራ ላይ ያለው የኤሌክትሪክ ታሪፍ በ2010 የፀደቀ ነው፡፡

በሥራ ላይ ያለው የኤሌክትሪክ ታሪፍ መጀመሪያ ሲወጣ በወቅቱ ከነበረው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ጋር ታሳቢ በማድረግ የተደረገ ጭማሪ ቢሆንም፣ አሁን ገበያ ውስጥ ያለው የግብዓት የዋጋ ንረት በታሪፍ ላይ ማስተካከያ ለማድረግ እንዳስገደደ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኃላፊዎች በተለያየ ጊዜ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

ተቋሙ በአገልግሎት አሰጣጡ ዙርያ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ያግዘኛል በማለት በአራት ዙር በአራት ዓመታት እንዲጠናቀቅ ተደርጎ በ2010 ይፋ ያደረገውን የታሪፍ ማስተካከያ፣ በታኅሣሥ 2014 የመጨረሻ ዙር ጭማሪ በማድረግ አጠናቆ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተመሳሳይ በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ ተግባራዊ ያደርገዋል የተባለው ማሻሻያ፤ የኢትዮጵያ ኢነርጂ እና ነዳጅ ባለሥልጣን በአጠቃላይ የያዘው የኢነርጂ ሪፎርም አካል መሆኑን ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት አዲስ በሚደርገው ማሻሻያ ዘርፉ ይበልጥ ለኢንቨስተሮች ሳቢ ይሆናል የሚል እቅድ መያዙንም የጋዜጣው ዘገባ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ አቅርቦት በአፍሪካ አህጉር በመጨረሻ ደረጃ ላይ ሦስት ሀገራት መካከል ውስጥ የምትጠቀስ ነች፡፡ በሀገሪቱ 56 ሚሊዮን ሕዝብ የኤክትሪክ ብርሃን አያገኝም፡፡ የኢነርጂ ኤክስፐርቶች እንደሚናገሩት፤ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ጭማሪ በመኖሪያ ቤቶችም ሆነ ፋብሪካዎች ወደ አማራጭ የኃይል አቅርቦት እንዲያማትሩ የሚገፋ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular