የስሪላንካ መንግሥት በኮቪድ ወቅት የሞቱ ሙስሊሞች የሃይማኖታቸው አስተምህሮ ከሚፈቅደው ባፈነገጠ መልኩ አስከሬናቸው እንዲቃጠል በማድረጉ በይፋ ይቅርታ ጠየቀ፡፡ የሃገሪቱ ሙስሊሞች ምክር ቤት ይቅርታውን ቢቀበልም፤ ለተፈጸመው በደል ማካካሻ እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡
የሀገሪቱ መንግሥት ካቢኔ በዛሬው እለት ወጣው መግለጫ፤ በኮቪድ19 ወረርሽኝ ወቅት አስገዳጅ ፖሊሲ በማውጣት ሙስሊሞች የሃይማኖታቸው አስተምህሮ ከሚፈቅደው ውጪ አስከሬናቸው እንዲቃጠል በማድረጉ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ ካቢኔው በመግለጫው በቀጣይ የሙስሊሞችም ሆነ ሌሎች ኅብረተሰብ ክፍሎች በቀብር ሥነ ሥርዐት ወቅት ተመሳሳይ የመብት ጥሰት እንዳይፈጸምባቸው የሚያደርግ ሕግ እንደሚዘጋጅም ገልጿል፡፡
እ.አ.አ በ2019 በተከሰተው የኮቪድ19 ወረርሽኝ የሞቱ የሀገሯን ዜጎች አስከሬን በሙሉ እንዲቃጠል አስገዳጅ ፖሊሲ በማውጣት ተግባራዊ ባደረገችው ስሪላንካ፤ የሙስሊም ዜጎች አሐዝ ከአጠቃላይ 22 ሚሊዮን ሕዝቧ 10 በመቶ ብቻ የሚይዝ ነው፡፡
የስሪላንካ መንግሥት በይፋ ሙስሊሞችን ይቅርታ መጠየቁን ተከትሎ፤ የስሪላንካ ሙስሊሞች ምክር ቤት ቃል አቀባይ ሂልሚይ አሕመድ ይቅርታውን እንደተቀበሉ ቢገልጹም፤ አሁንም ድረስ በሀገሪቱ የሚገኙ ሙስሊሞች ከድርጊቱ ድንጋጤ እንዳላገገሙ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ፖሊሲው ተግባራዊ እንዲደረግ ተባብረዋል ያሏቸው ሁለት ምሁራን ላይ ክስ እንደሚመሠርቱ ጠቁመዋል፡፡
በወቅቱ የስሪላንካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጎታባያ ራጃፓክሳ፤ በቅርቡ ባሳተሙት መጽሐፍ አሁን በሙስሊሞች ምክር ቤት ክስ ይጠብቃቸዋል በተባሉ ምሁራን ምክር ላይ ተመሥርተው የኮቪድ19 ሟቾች አስከሬን እንዲቃጠል ትእዛዝ ማስተላለፋቸውን ገልጸዋል፡፡
የሙስሊሞች ምክር ቤት ቃል አቀባዩ፤ በወቅቱ ከእስልምና አስተምህሮ ውጭ የተተገበረው ፖሊሲ በ40 ቀን ሕጻን ላይ ጭምር ተፈጻሚነት የነበረው መሆኑን በማስታወስ፤ በሕጻኑ ወላጆች ላይ ያሳረፈው አእምሯዊ ጠባሳ ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ቃል አቀባዩ በሙስሊሞች ላይ ለደረሰው ሁሉ ማካካሻ እንጠይቃለን ማለታቸውንም አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል፡፡
በስሪላንካ በኮቪድ ወቅት የሞቱ ሙስሊሞች አስከሬን እንዲቃጠል መደረጉ በሀገሪቱ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ትችት በማስከተሉ በመሃል እንዲቆም ተደርጓል፡፡ የወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ውሳኔውን ያጠፉት የቀድሞው የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካን በ2021 ስሪንካን በጎበኙበት ወቅት ባቀረቡት ጥያቄ መሆኑ ይነገራል፡፡ ከዚህ ውሳኔ በኋላ በኮቪድ19 የሞቱ ሙስሊሞች የቀብር ሥነ ሥርዐት ሲከናወን የነበረው ከከተማ ራቅ ባለ ሥፍራ በከፍተኛ ወታደራዊ አጀብ ነበር፡፡ በቀብር ሥነ ሥርዐቱ ላይ ሟች ቤተሰቦች እንዳይገኙ ተከልክሎ ነበር፡፡ በስሪላንካ በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ 672 ሺህሕ ሰዎች ውስጥ፤ 16 ሺሕ 897 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፡












