Homeዜናና ወቅታዊዜናሐማስ እና ፈትሕን ጨምሮ 14 የፍልስጤም ኃይሎች የጋራ ትብብር ስምምነት ተፈራረሙ

ሐማስ እና ፈትሕን ጨምሮ 14 የፍልስጤም ኃይሎች የጋራ ትብብር ስምምነት ተፈራረሙ

ሐማስ እና ፈትሕን ጨምሮ 14 የፍልስጤም ኃይሎች በመሃላቸው ያለውን ልዩነት ወደ ጎን በመተው በጋራ ለመንቀሳቀስ የሚያስችላቸውን የትብብር ስምምነት በቻይና ተፈራርመዋል፡፡ ኃይሎቹ ስምምነቱን የፈጸሙት በቻይና አደራዳሪነት ነው፡፡

ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 16/2016 በቻይና የተፈረመውን የቤጂንግ ስምምነት ያደራደሩት የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ መሆናቸውንም የሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡ ሐማስ እና ፈትሕን ጨምሮ ኃይሎቹ ዛሬ ስምምነቱን የተፈራረሙት፤ ከእሑድ ሐምሌ 14 አንስቶ ሲያደርጉት በቆዩት ድርድር መዝጊያ ሥነ ሥርዐት ላይ ነው፡፡

ከስምምነቱ በኋላ የተናገሩት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ኃይሎቹ ከጋዛ ጦርነት ማብቃት በኋላ ጊዜያዊ መንግሥት ለመመሥረት መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዛሬው እለት በተካሄደው የድርድር መዝጊያ ሥነ ሥርዐት ላይ የተናገሩ አንድ ዲፕሎማት፤ የጋራ ስምምነት የፈረሙት የፍልስጤም ኃይሎች ለእርቅ ዝግጁ ናቸው ብለዋል፡፡

ከቡድኖቹ መካከል ሐማስ እና ፈትሕ በሚያዝያ ወር በተመሳሳይ ልዩነታቸውን ለመፍታት በቻይና ድርድር ሲያደርጉ ነበር፡፡ ሐማስ እና ፈትሕ በተለይ ባለፉት ዓመታት በተቀናቃኝነት ቆይተው ከመስከረም መጨረሻ ወር አንስቶ እስራኤል በጋዛ የጀመረችው ዳግም ጥቃት ለንግግር በር ከፍቶላቸዋል፡፡

የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት ሊን ጂያን፣ በወቅቱ የሁለቱ ቡድኖች መሪዎች ያካሄዱት ውይይት በመሃላቸው ያለውን ልዩነት በንግግር ለመፍታት ፍቃደኝነታቸውን ገልጸዋል ብለው ነበር፡፡

በቻይና አደራዳሪነት ንግግር ጀምረው በዛሬ እለት ከሌሎች ኃይሎች ጋር የጋራ ስምምነት የፈረሙት ሐማስ እና ፈትሕ፣ በተያዘው ዓመት መጀመሪያ በተመሳሳይ የጋራ መንግሥት ስለማቋቋም በሩስያ መዲና ሞስኮ መክረው ነበር፡፡

 በፍልስጤም ኃይሎች መካከል የተካሄደውን ድርድር የመራችው ቻይና፤ የፍልስጤም ችግር የሚፈታው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገርነት ዕውቅና ስታገኝ ነው የሚል አቋም በማራመድ ትታወቃለች፡፡  ሀገሪቱ እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመው ጥቃት እንዲቆም የተኩስ አቁም እንዲደረግ ስትወተውትም የቆየች ነች፡፡

ሐማስ እና ፈትሕ በፍልስጤም መሬት ተጽዕኗቸው የጎላ የፖለቲካ ኃይሎች ሲሆኑ፤ በእስራኤል ሀገርነት ላይ የተለያየ አቋም በማራመድ ይታወቃሉ፡፡ ከቡድኖቹ ውስጥ ሐማስ ለእስራኤል ዕውቅና የማይሰጥ ሲሆን፣ ፈትሕ በበኩሉ የሀገርነት ዕውቅና ይሰጣል፡፡ ቡድኖቹ የፍልስጤም እና እስራኤል ልዩነት በሚፈታበት የትግል ስልት ላይ እንዲሁ ልዩነት አላቸው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular