የዓለም ሙስሊሞች ናፍቆት የሆነው ሐጅ፤ ለዓመት ቀጠሮ ይዞ ተሸኘ፡፡ 12 ሺሕ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ለክንውኑ ወደ ቅድስቲቱ መካ ከተማ ያመሩ ምዕመናን፤ ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ይገኛሉ፡፡
ሐጅን ያስተናገደው ዙልሒጃ ወር ሲሸኝ፤ ቀጣዩ ሳምንት ዐዲስ ዓመት ይሆናል፡፡ በተጀመረው ዐዲስ ሳምንት የመጨረሻ ቀናት ከተከበሩ ወራት አንደኛው ሙሐረም ይጀምራል፡፡ ከሙሐረም መምጣት ጋር ቀጣይ ቀናት ካዕባ በዐዲስ ልብስ ሊያጌጥ ሽር ጉድ ተጀምሯል፡፡

ሳዑዲ ዐረቢያ በቀጣይ የምትቀይረውን የካዕባ ልብስ (ኪስዋ) ከጥቂት ሳምንታት በፊት የሐጅ ቀናት ሲቃረቡ ከፍ አድርጋው ነበር፡፡ ሀገሪቱ በዘንድሮ ዓመት ኪስዋውን ከመሬት ከፍ ለማድረግ 36 ባለሞያዎችን ከአስር “ክሬን” ጋር መድባ ነበር፡፡ ባለሞያዎቹ ልብሱን ከፍ አድርገው በአራቱም ማዕዘን በነጭ የጥጥ ጨርቅ እንዲሸፈን (ኢህራም) አድርገውታል፡፡
ኢህራም የተደረገው ኪስዋ በየዓመቱ የሙሐረም ዋዜማ ላይ የሚቀየር ነው፡፡ እንደ ቀድሞው ቢሆን ኪስዋ የሚቀየረው ባለፈው ዙልሒጃ ወር 9ኛው ቀን የነበረ ቢሆንም በቅርብ ጊዜያት ወደ ሙሐረም ዋዜማ መጥቷል፡፡ ባለፈው ዓመት በኪስዋ ቅያሪው ወቅት 100 የዕደ ጥበብ ባለሞያዎች ተሳታፊ ሆነው ነበር፡፡

ኪስዋ የዓለማችን ውዱ ልብስ ነው፡፡ የልብሱ ክብደት 850 ኪሎ ግራም ሲመዝን፣ ወጪው ደግሞ 6.5 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡
ኪስዋ ሲዘጋጅ ቢያንስ 200 ባለሞያዎች ይሳተፋሉ፡፡ የኪስዋ 670 ኪሎ የሚመዝነው ጥቁር ሐር ነው፡፡ በዚህ ሀር ላይ ለሚጻፉ የቁርኣን አንቀፆች 120 ኪሎ 21 ካራት ወርቅ እንዲሁም 100 ኪሎ ግራም ብር ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












