የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) ለሐጅ ክንውን ሳዑዲ ዐረቢያ ያቀኑ ኢትዮጵያውያን በቀጣይ ሁለት ሳምንት ተጠቃለው እንደሚመለሱ አስታወቀ። ምክር ቤቱ እስካሁን ድረስ ወደ ሀገር ቤት የተመለሱ ኢትዮጵያውያንን ቁጥር ይፋ አድርጓል።
ምክር ቤቱ በዘንድሮው ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ እንዲሳተፉ 12 ሺሕ ኢትዮጵያውያን ምዕመናንን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ መላኩ የሚታወቅ ነው።
ሚንበር ቲቪ ከምክር ቤቱ ኃላፊዎች እንደሰማው፣ የሐጅ ክንውኑ መጠናቀቁን ተከትሎ ምዕመናኑ በሔዱበት ቅደም ተከተል መሠረት እየተመለሱ ነው። እንደ ምክር ቤቱ ኃላፊዎች ከሆነ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 24፣ 2016 ድረስ 4 ሺሕ 600 ሑጃጅ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።
በቀጣይ ቀናትም ሑጃጁን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራ እንደሚቀጥል የጠቆሙት የመጅሊስ ኃላፊዎች፣ ምዕመናኑ ወደ ኢትዮጵያ የመጨረሻ ቀን መቼ እንደሚሆንም ለሚንበር ቲቪ ገልፀዋል። ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱበት የመጨረሻ ቀን ሐምሌ 6/2016 እንደሚሆን ተገልጿል።
ከኢትዮጵያውያን መካከል በራሳቸው የበረራ ትኬት የቆረጡ ምዕመናን መጅሊስ ካስቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ ቀደም ብሎ ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው።
ከሑጃጅ ጋር በተገናኘ ሌላ መረጃ በዘንድሮው የሐጅ ክንውን ወቅት ኢትዮጵያውያን ሐጃጆች ውስጥ በድምሩ 10 ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸው ማለፉን ምክር ቤቱ በዛሬው እለት ገልጿል። አሥሩ ኢትዮጵያውያን ሑጃጅ በሙሉ በመካ፣ መስጂደል ሐረም ላይ ሶላተል ጀናዛ ተሰግዶባቸው የቀብር ሥርዓታቸው ተፈጽሟል ተብሏል።
የአምስቱ ሐጃጆች ሕይወት የሐጅ ሥርዓት ከመጀመሩ በፊት ማለፉ ሲገለፅ፣ የሌሎቹ ሕይወት ያለፈው በአረፋ ወቅት ነው።
ከሟቾቹ መካከል ስድስቱ ሑጃጅ በድንገተኛ ሕመም፣ ሁለቱ በክፍላቸው ውስጥ ሞተው የተገኙ ሲኾን፣ አንድ ሐጃጅ በመኪና አደጋ፣ አንድ በካንሰር፣ እንዲሁም ሌላ አንድ ሐጃጅ በሕመም ምክንያት እንደሞቱ ምክር ቤቱ አስታውቋል።
በ1445 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ከመላው ዓለም ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ቅድስቲቱ መካ ከተማ ደርሰው ክንውኑን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ይገኛሉ። (ሚንበር ቲቪ)












