የልዩ ፍላጎት ላላቸው ሕፃናት ወላጆች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመጋፈጥ ይረዳል የተባለ ሥልጠና ተሰጠ፡፡ ወላጆቹ ሥልጠናውን የወሰዱት ለሦስት ወራት መሆኑ ተገልጧል፡፡
ላለፉት ሦስት ወራት ሲሰጥ የቆየው ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሕፃናት ወላጆች ሥልጠና ቅዳሜ ሰኔ 22/2016 ሲጠናቀቅ፣ 30 ወላጆች መሳተፋቸውን ሥልጠናውን የሰጠው ሲኪስቲ ናይን የማማከር እና ሥልጠና ማዕከል ለሚንበር ቲቪ ገልጧል፡፡
የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢብራሂም ሙነወር እንደገለጹት፣ ለሦስት ወራት በነበራቸው ቆይታ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሕፃናት ወላጆች የተለያዩ ሥልጠናዎችን አግኝተዋል፡፡ እንደ አቶ ኢብራሂም ከሆነ ለወላጆች የተሰጠው ሥልጠና አምስት ርእሰ ጉዳዮችን ያካተተ ነው፡፡
ከአምስቱ የሥልጠና ርእሶች ውስጥ በጠባይ መግራት ላይ የሚያተኩረው ቢሄቪየራል ቴራፒ፣ በንግግር ላይ ስፒች ቴራፒ እንዲሁም ስለ አመጋገብ ይገኝበታል፡፡ ወላጆች በሥልጠናው የልጆችን ጠባይ ለመግራት እንደሁም ለአመጋገብ ጠቃሚ ክሕሎት መቅሰማቸውን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
ለሦስት ወራት የቆየው ሥልጠና ሲጠናቀቅ የመዝጊያው ሥነ ሥርዐት በአዲስ አበባ ከተማ መካኒሳ አካባቢ በሚገኘው ቢላሉል ሐበሺ አዳራሽ ተከናውኗል፡፡

ሥልጠናውን የሰጠው ሲኪስቲ ናይን የማማከር እና ሥልጠና ማዕከል በቀጣይ ለሌሎች ወላጆች ሥልጠናውን መስጠት እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
ሲኪስቲ ናይን የማማከር እና ሥልጠና ማዕከል በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የማማከር አገልግሎት የሚሰጥ ግል ድርጅት ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












