የዛሬ ዓመት በዚህ ሰዓት ፍልስጤማዊቷ ሻይማ አቡአላታ፣ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ጋዛ ሦስተኛ ዓመት የኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ተማሪ ነበረች፡፡ ያን ጊዜ የሻይማ ሕይወት በዩኒቨርሲቲዋ ውስጥ ያጠነጠነ ነበር፡፡ ከቤት ወደ ዩኒቨርሲቲ፤ ከዩኒቨርሲቲ ደግሞ ወደ ቤት ተመልሳ የሠፈር ሰው እና ቤተ ዘመድ ጥየቃ ብትጓዝ ነው፡፡
ከአንድ ዓመት በኋላ የሻይማ አቡአላታ ሕይወት ትዝታው ብቻ ቀርቷል፡፡ ሸጃያ አካባቢ የሚገኘው የወላጆቿ መኖሪያ ቤት በእስራኤል ጥቃት እንዳልነበረ ሆኗል፡፡ ቤተሰቦቿም ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ አሁን የሻማ የዩኒቨርሲቲ ትምሕርት የማይታሰብ ነው፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ወደ ቤት መመላለሷ፣ ዘመድ እና የሠፈር ሰው ጥየቃ መሔዷም ቀርቷል፡፡
አሁን ሻይማ የምትገኘው በጋዛ ማዕከላዊ ክፍል በሚገኘው ዴር አል ባላህ አካባቢ በተጨናነቀ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ነው፡፡ እዚህ መኖር ከጀመረች ስድስት ወራት አለፉ፡፡ በጣቢያው መብራት እና ንጹሕ የመጠጥ ውሃ የለም፡፡ እርሷና ሌሎችም በጣቢያው ንጹሕ ውሃ ማግኘት የሚቻል ባይሆንም ራሳቸውን በሌላ መንገድ ማንጻት እንዳለባቸው በማሰብ አዲስ ሐሳብ አፈለቁ፡፡ ሻይማ እንደምትለው አዲሱ ሐሳብ ያሉበትን በማስረሳት የቀደመ ኑሯቸውን የሚያስታውሳቸው፤ ከዚያም ሲያልፍ መንፈሥን ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡

ሻይማና የተፈናቃይ ጣቢያው ባልንጀሮቿ መጀመሪያ በራሳቸው ድንኳን ውስጥ ቁርኣን ማስቀራት ጀመሩ፡፡ የቁርኣን ጥናቱን የጀመሩት በሕፃናት ነው፡፡ ቀስ በቀስ ሌሎችም እየተሰባሰቡ ሲመጡ ግን የማስፋፋት እቅድ በመንደፍ ለምን በድንኳን መስጂድ አንሠራም አሉ፡፡ በሐሣብ ብቻ አልተገቱም፤ አደረጉት፡፡ አሁን በቁርኣን ጥናት ድንኳኑ ውስጥ የ70 እና 80 ዓመት አዛውንት ቁርኣን ሲቀሩ ማግኘት አዲስ ነገር አይሆንም፡፡
ሻይማ ቁርኣን መቅራት እና ማስቀራታቸው በምን ያህል መጠን ብርታት እንደሆናቸው ደጋግማ የምታስረዳው ጉዳይ ሆኗል፡፡ እርሷም ሆነ ሌሎች የእስልምና ወንድም እና እሕቶቿ በተደጋጋሚ ከሞት መትረፋቸውን የምታስታውሰው ሻይማ፤ ሞት መቼ ደጃፏን እንደሚያንኳኳ ስለማታውቅ ቀድማ መዘጋጀት እንዳለባት ታምናለች፡፡ መጨረሻዋ ማሳመር የምትመኘው ሻይማ፣ ድንገት ሞት ቢመጣ እንኳን ከቁርኣን ጋር ባለንበት እንዲሆን እንፈልጋለን ብትላለች፡፡

እነ ሻይማ በማዕከላዊ ጋዛ የድንኳን መስጂድ ባስጀመሩት የቁርኣን ጥናት በየእለቱ የሚሳተፉ ሁሉም የሚደጋግሙት አንድ ነገር አለ – “ቁርኣን መልካም ወዳጅ ሆኖናል” ይላሉ፡፡ በቁርኣን ድንኳኑ ከቁርኣን ጋር የሚውሉ ፍልስጤማዊያን ወደ ቁርኣን ይበልጥ በቀረቡ ቁጥር፣ ያሉበት ሰቆቃ የሚያበቃበት ጊዜ እየቀረበ መሆኑን ያምናሉ፡፡ እነ ሻይማ በቁርኣን የጋዛን ጨለማ ረስተው፤ በብርሃን ተሞልተዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












