የሐላል ገበያ ምርቶች ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ውጪ ባሉ ተጠቃሚዎች ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል የተባለው ‘በሐላል ሞሮኮ ፎረም’ ላይ ነው፡፡ በሐላል ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በተጠቃሚዎች ተማራጭ የሆኑት ከጥራት እና ጤና አንጻር እንደሆነም ተገልጧል፡፡
‘የሐላል ሞሮኮ ፎረም’ ትናንት ሐሙስ በካዛብላንካ ከተማ ሲካሔድ፣ ከሐላል ኢንዱስትሪ ጋር በተገናኘ በሞሮኮና በሌችም የዓለም ሀገራት ያሉ ተመክሮዎች ዳሰሳ ተደርጎባቸዋል፡፡ በፎረሙ መድረክ ላይ የተናገሩት የሞሮካዊያን ኤክስፖርተሮች ማኅበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ሐሳን ኤል ሰንቲሲ፣ በሐላል ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ከሙስሊሙ ውጪ ባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተመራጭ እየሆኑ መምጣታቸውን በመጠቆም፣ ተጠቃሚዎች ምርቶቹን ተመራጭ ያደረጉትን ምክንያትም አብራርተዋል፡፡
እንደ ፕሬዝዳንቱ ከሆነ ከሙስሊሙ ውጭ ያሉ ተጠቃሚዎች በሐላል አግባብነት ተመዝነው የጥራት ማረጋገጫ የተሰጣቸውን ምርቶች ከጤና እና ጥራት አንጻር ይመርጣሉ፡፡ ሐሳን ልማድ ይህ በተለይ በእስያ እና ፓሲፊክ ቀጣና ውስጥ በሚገኙ ሀገራት እየጨመረ መጥቷል ሲሉ በምሣሌነት ጠቅሰዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አያይዘው የሐላል ማረጋገጫ ያገኙ ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዓማኒነት ደረጃቸው ከፍ እያለ ምምጣቱን የጠቀሱ ሲሆን፣ ገበያው እየሰፋ እንደ ብራዚል ዐይነት የሙስሊሞች ቁጥር አነስተኛ የሆነባቸው ሀገራት ሳይቀሩ በሐላል ኤክስፖርት ድርሻቸው ግዙፍ እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡ ሐሳን የሐላል ገበያ ከሙስሊሙ የማኅበረሰብ ክፍል ውጪ ባሉትም ጭምር ተመራጭ የሆነበትን ምክንያት ሲያብራሩ፣ ሃይማኖታዊ መሥፈርት ከማሟላቱ በተጨማሪ ከንጽሕና አኳያ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ አሟልቶ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡
ሐሳን በኤክስፖርት ከፊት ተቀምጣለች በሚል የጠቀሷት ብራዚል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሐላል ሥጋ በማቅረብ በቀዳሚው ረድፍ ላይ የተቀመጠችው ለእስላማዊ ትብብር ድርጅት አባል ሀገራት ብቻ በምታቀርበው 14.04 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የሐላል ሥጋ ነው፡፡
የሐላል ሥጋ አቅርቦት በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ የሚገኘው ሐላል ኢንዱስትሪ አንደኛው ዘርፍ ነው፡፡ ሰባት ዘርፎችን የሚያቅፈው ይህ ኢንዱስትሪ፤ በሥሩ ምግብን ጨምሮ እስላማዊ ፋይናንስ፣ ሐላል ቱሪዝም፣ ሐላል ፋሽን፣ ሐላል ሚዲያ እና መዝናኛ፣ የመድኃኒት እና ሐላል መዋቢያዎችን የሚያካትት ነው። (ሚንበር ቲቪ)












