የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በነገው እለት የወረቀት መታወቂያ መስጠት በይፋ እንደሚያቆም አስታወቀ፡፡ በከተማ አስተዳደሩ የወረቀት መታወቂያ መስጠት የሚያቆመው ከ75 ዓመት በኋላ መሆኑ ተገልጧል፡፡
የከተማዋ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ፤ በስሩ ካሉት 119 ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ 104ቱ ዲጂታላይዝድ ተደርገው የነዋሪነት መታወቂያ በዲጂታል ሲሰጡ ቆይተዋል ተብሏል፡፡
14 ወረዳዎች ደግሞ ላለፉት አራት ዓመታት በመሠረተ ልማት እና ተመሣሣይ ምክንያት የነዋሪነት መታወቂያን እና ሌሎች ማስረጃዎችን በወረቀት እየሰጡ ቆይተዋል።
የከንቲባ ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው፣ የዲጂታል መታወቂያ መስጠት ባልተጀመረባቸው የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ስድስት ወረዳዎች፣ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ሦስት ወረዳዎች፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አራት እንዲሁም የኮልፌ ክፍለ ከተማ አንድ ወረዳ መሆናቸውን ዘርዝሯል፡፡ እነዚህ ወረዳዎች አስፈላጊው ሁሉ እንዲሟላላቸው በማድረግ ወደ ዲጂታል እንዲሻገሩ ዝግጅት ተጠናቋል ተብሏል፡፡
ከዚህ ቀደም የተሰጡ የአገልግሎት ግዜያቸው ያላበቃ የወረቀት መታወቂያዎች አገልግሎት እየሰጡ ይቆያሉ የተባለ ሲሆን፣ ዝግጅቶች ተጠናቀው በቅርብ ወራት ነዋሪዎች ወደ የሚኖሩበት የወረዳ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት በመቅረብ እንዲቀይሩ እንደሚደረግ ተነግሯል። ይሁንና አሁንም ይህን አገልግሎት ለሚፈልጉ አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑን ኤጀንሲው አስታውቋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በዘመናዊ የከተማ አስተዳደር የከተማ የነዋሪነት መታወቂያን በተደራጀ መልኩ መስጠት ከተጀመረ ከ75 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡












