ሞትን በፈገግታ


ሐጅ ሲጠናቀቅ ምዕመናንም ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ነው። ያለፉትን ጥቂት ሳምንታት በቅዱሳኑ መካ እና መዲና ከተሞች የሰነበቱ ኢትዮጵያውያንም አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል። በርግጥ እስካሁን ወደ ከተማዋ የተመለሱት ትኬት በግላቸው የቆረጡ መሆናቸው ታውቋል። በመጅሊስ ሥርዓት ቀዳሚዎቹ ተመላሾች የሚገቡት ዛሬ ረቡዕ ይሆናል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

ከሐጅ ክንውን መጠናቀቅ በኋላ ለሥርዐቱ እምብዛም ሽፋን የማይሰጡ የአውሮፓ እና አሜሪካ መገናኛ ብዙኃንን አትኩሮት ስቦ የነበረው፤ ምዕመናን ለሐጅ ተጉዘው ሕይወታቸው ማለፉ ሆኗል። በረሐማዋ ሳዑዲ ከተቀበለቻቸው እንግዶች መካከል 1 ሺሕ 301 ሰዎች ከምድር ሕይወት ተለይተዋል። ይህን አሐዝ የሳዑዲ ጤና ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ባለፈው እሑድ አረጋግጠዋል። ለበርካታ ምዕመናን ሞት ምክንያት የሆነው መጠኑ በጣም ከፍ ብሏል በሚል ተደጋግሞ ሲነገር የሰነበተው ሙቀት ነው።

የምዕመናን ኅልፈት ዜና መውጣት ከጀመረ ወዲህ ተደጋጋሚ ሽፋን የሰጡት አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እና አርኤፍአይ፣ ሲኤንኤን እና ኒውዮርክ ታይምስ እንዲሁም ቢቢሲና ሌሎችም፤ በተለይ በዕድሜ የገፉ ሟቾች ከቤተሰቦቻቸው ጋር የነበራቸውን የመጨረሻ ሰዓታት ንግግር አስነብበዋል። የዕድሜ ዘመን ምኞታቸውን ለመሙላት በቅዱሳኑ ከተሞች መካ እና መዲና ተገኝተው በመንፈሥ ከፍ ለማለት የታደሉት ምዕመናን፣ በመጨረሻዎቹ ሰዓታት በድካም ዝለው በፀሓይ ንዳድ ቢገረፉም የሚያማርሩ አልነበሩም። ሞትን በፈገግታ ተቀብለውታል።

ለዚህ ምሥክር የሚመስለው እናት እና አባታቸውን ያጡ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ለመገናኛ ብዙኃኑ በሰጡት ቃል ተመሳሳይ ንግግር ተስተጋብቷል። ልጆቹ “አባቴ/እናቴ የል(ቡ)ቧ ነው የሞላለ(ላ)ት” ብለዋል። የልባቸው ምኞት የደረሰው ወላጆች ‘ሞቴን ቅዱሳኑ ሥፍራ አድርግልን’ ብለው ሲማጸኑ የቆዩ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው የሆኑት ኢንዶኔዥያዊው የ86 ዓመት አዛውንት ጋቲዮ ወንሶ ናቸው፡፡ ልጃቸው ሄሩ ለሲኤንኤን እንደተናገረው፣ አባትየው ጋቲዮ ሲናፍቁት ለቆዩት የሐጅ ክንውን የተመዘገቡት ከስድስት ዓመት በፊት እ.አ.አ በ2018 ነበር፡፡ ኢንዶኔዥያዊው አባት የናፈቁበት ሥፍራ ደርሰው ኅልፈታቸው የሆነው ሚና ውስጥ ድንኳን ውስጥ በተኙበት ነው፡፡

ልጅየው እንደሚለው አባት ጋቲዮ ከምድር ሕይወት ከመለየታቸው አስቀድሞ የጤናቸው ሁኔታ መልካም የሚባል ነበር፡፡ በድንገት ግን በዚያው በተኙበት አሸለቡ፡፡ ልጅየው ሄሩ አባቱ በድንገት ቢለዩትም ሐዘኑን የሚያስረሳው ጉዳይ አለ፡፡ አባትየው የተቀበሩት መካ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ሄሩ ስለ ጉዳዩ ለአሜሪካው መገናኛ ብዙኃን “መካ ውስጥ በመቀበሩ ደስተኛ ነኝ” ብሎታል፡፡

ኢንዶኔዥያዊው ሄሩ ስለ አባቱ የተናገረው ጉዳይ በተመሳሳይ ወላጆቻቸው በተለዩዋቸው ግብጻዊያንም ይሁን ናጄሪያውያን እየተደጋገመ ነው፡፡ የሲኤንኤን ጋዜጠኛ የኢንዶኔዥያዊው ሄሩ ቀጣይ እቅድ ምን እንደሆነ ጠይቆት ነበር፡፡ የሄሩ ምላሽ የነበረው “ሐጅ ማድረግ” የሚል ነበር –  በዚያውም አባቱ ያረፉበትን ማየት ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular