የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) ትናንት ሰኞ ሰኔ 17/2016 ማለዳ ላይ ባወጣው መረጃ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ በግል ትኬት የቆረጡ ምዕመናን የበረራ መስተጓጎል እንደገጠማቸው አስታውቆ ነበር፡፡ ምክር ቤቱ የምዕመናኑ በረራ የተስተጓጎለው ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ሲገቡ ፓስፖርታቸውን የተቀበላቸው ኩባንያ በሰዓቱ ደርሶ ፓስፖርታቸውን ባለመመለሱ ሳቢያ መሆኑንም ገልጧል፡፡ የበረራ መስተጓጎል ገጥሟቸዋል የተባሉት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 93 ነው፡፡
ምክር ቤቱ ምዕመናኑን በተመለከተ በተመሳሳይ ቀን ባወጣው ሌላ መረጃ ከሳዑዲ የሐጅ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ሑጃጅ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ሁነታዎችን እንዳመቻቸ አስታውቋል።
ቀደም ብሎ በተሰጠው መረጃ ምክር ቤቱ አጠቃላይ የጉዞ መስተጓጎል የገጠማቸው ሑጃጅ ቁጥር 93 እንደነበር ቢገልፅም፣ ኋላ ላይ ባወጣው መረጃ የተመላሾቹን ቁጥር በሦስት በመቀነስ 90 ናቸው ብሏል፡፡
ከእነዚህ 90 ሑጃጅ መካከል አንደኛዋ ምዕመን “በግል ምክንያት” በመዘግየታቸው አለመካተታቸው ተገልጧል፡፡
ሚንበር ቲቪ ዛሬ ንጋት ላይ ከገቡ ሐጅ አድራጊ ማረጋገጥ እንደቻለው በምክር ቤቱ ሁለተኛ መረጃ የተጠቀሱት 89 ሑጃጅ አዲስ አበባ ደርሰዋል፡፡ በግል ምክንያት ዘግይተዋል የተባሉት ምዕመንም ዛሬ አመሻሹ ላይ እንደሚመለሱ ተሰምቷል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የበረራ መስተጓጎል ገጥሟቸው ነበር ያላቸውን በግል ትኬት የቆረጡ ኢትዮጵያውያን ሑጃጅ ወጪ ተሸፍኗል ያለው በሳዑዲ ዐረቢያ የሐጅ ሚኒስቴር ነው፡፡
ለዘንድሮው የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ቀዳሚዎቹ ሑጃጅ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የተጓዙት ግንቦት 13/2016 እንደነበር ይታወቃል፡፡ ምክር ቤቱ በተያዘው ዓመት ለክንውኑ የላካቸው ምዕመናን አሐዝ 12 ሺሕ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት በተጠናቀቀው የሐጅ ሥነ ሥርዐት ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሑጃጅ ከመላው ዓለም ተሳታፊ መሆናቸውን የሳዑዲ ዐረቢያ የሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡ ክንውኑ መጠናቀቁን ተከትሎ ያለፉትን ሳምንታት በቅዱሳኑ መካ እና መዲና ከተሞች ያሳለፉ ምዕመናን ወደ ሀገራቸው መመለስ ከጀመሩ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡
ወደ ሀገራቸው ከተመለሱት ውስጥ ከኢትዮጵያ የተጓዙ ምዕመናን ይገኙበታል፡፡ ከመጅሊስ ሥርዐት ውጪ በግል ትኬት የቆረጡ ምዕመናን ወደ ኢትዮጵያ መመለስ የጀመሩት ባለፈው ሳንምት ሐሙስ ነው፡፡ በግል ትኬት በመቁረጥ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱት በተጨማሪ በመጅሊስ ሥርዐት ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ ምዕመናን የመጀመርያ በረራ ነገ ረቡዕ ሰኔ 19/2016 ይከናውናል ተብሏል፡፡
የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በነገው እለት በረራ የሚያከናውኑት፤ ቀድመው ከኢትዮጵያ ቀድመው ለሐጅ ሥነ ሥርዐት የተነሱ ናቸው ብሏል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












