በእስላማዊ መርሆች መሠረት አገልግሎት የሚሰጡ የግብጽ ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ 10 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ተገለጸ፡፡ የባንኮቹ ተቀማጭ ባለፈው ዓመት ከነበረው በ23.5 በመቶ ጭማሪ አስመዝግቧል ተብሏል፡፡
የግብጽ እስላማዊ ባንኮች ተቀማጭ ባለፈው ዓመት ከነበረበት ዕድገት በማስመዝገብ 10.56 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ይፋ ያደረገው የግብጽ እስላማዊ ፋይናንስ ማኅበር ነው፡፡ የሀገሪቱ እስላማዊ ባንኮች አጠቃላይ ተቀማጭ ባለፈው ዓመት 8.56 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር አስታውሷል፡፡
የግብጽ እስላማዊ ፋይናንስ ማኅበር ከሀገሪቱ እስላማዊ ባንኮች ተቀማጭ በተጨማሪ በሀገሪቱ ፍቃድ በወሰዱ እስላማዊ ባንኮች ውስጥ የተደረገው የገንዘብ ዝውውር መጠን በተመሳሳይ ዕድገት ማሳየቱን አስታውቋል፡፡ እንደ ማኅበሩ ከሆነ በባንኮቹ መካከል የተደረገው የገንዘብ ዝውውር መጠን 701 ቢሊዮን የግብጽ ፓዉንድ (14.5 ቢሊዮን ዶላር) መሆኑንም አመልክቷል፡፡

የግብጽ እስላማዊ ባንኮች ያደረጉት የገንዘብ ዝውውር መጠን ያስመዘገበው ዕድገት 28.8 በመቶ ነው፡፡
የግብጽ ብሔራዊ ባንክ በአሁኑ ወቅት ለ14 ባንኮች በሸሪዓ ላይ የተመሠረተ አገልግሎት እንዲሰጡ ፍቃድ ሰጥቷል፡፡ ከባንኮቹ መካከል ሦስቱ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ባንኮች አል በረካ ባንክ ኢጂፕ፣ ፈይሰል ኢስላሚክ ባንክ ኦፍ ኢጂፕት እና አቡ ዳቢ ኢስላሚክ ባንክ ኢጂፕት ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ 11 እስላማዊ ባናኮች በቅርንጫፍ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡
ከእስላማዊ ባንኮቹ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል የተባለው ፈይሰል ኢስላሚክ ባንክ ኦፍ ኢጂፕት ሲሆን፣ ከአጠቃላይ የግብጽ እስላማዊ ባንክ ዘርፍ 31 በመቶ የገበያ ድርሻ ይዟል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












