Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችበደላላ ለሐጅ ወጥተው የቀሩት

በደላላ ለሐጅ ወጥተው የቀሩት

የሐጅ ክንውን መጠናቀቁን ተከትሎ በወጡ የሞት ዜናዎች ተደጋግመው የተጠቀሱት ግብጻዊያን ሆነዋል፡፡ በሀገሪቱ ባለሥልጣናት ይፋዊ ማረጋገጫ ያልተሰጠባቸው አሐዞች እንደሚያሳዩት ከ650 በላይ ግብጻዊያን ለሐጅ ባቀኑበት ከምድር ሕይወት ተሰናብተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 630 የሚሆኑት ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የገቡት በሐጅ ቪዛ ሳይሆን በጉብኝት አልያም በሌሎች የቪዛ ዐይነቶች ነው፡፡

ምዕመናኑ ይህን አማራጭ የተጠቀሙት በመደበኛ የሐጅ አማራጭ ለጉዞ የሚከፈለው ገንዘብ (ስድስት ሺሕ ዶላር) መሸፈን የሚችሉት ባለመሆኑ ነው፡፡ ጉዞውን ያደረጉትም ‘የክፍያውን ገንዘብ ቀንሰን የሐጅ ጉዟችሁን እናመቻቻለን’ በሚሉ ደላሎች በኩል ነው፡፡

የአምስት ልጆች እናት የሆኑት የ70 ዓመቷ እናት ኢፌንዲያ ለሐጅ የተጓዙት በዚህ መንገድ ነበር፡፡ የመጀመርያ ልጃቸው ሰዒድ ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገረው፣ እናቱ የረዥም ዘመን ሕልማቸውን ለመፈጸም ወርቃቸውን ሸጠዋል፡፡

ኢፌንዲያ የግብጽ ሐጅ መስሪያ ቤት ከሚያስከፍለው ‘ግማሹን ከሰጠችሁኝ ሳዑዲ አድርሼ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል የሚሰጠውን አገልግሎት ታገኛላችሁ’ ያላቸውን ደላላ በማመን ጉዟቸውን አድርገዋል፡፡

በርግጥ ደላላው በጉብኝት ቪዛ ሳዑዲ ዐረቢያ አድርሷቸዋል፡፡ ያገኙት አገልግሎት ግን ቀድሞ በገባው ቃል መሠረት የተከናወነ አልነበረም፡፡ መካ ከተማ ደርሰው ወደ አረፋ ተራራ ሲያመሩ የጫናቸው አውቶብስ ከመድረሳቸው አስቀድሞ 12 ኪሎ ሜትር ላይ አራግፏቸው ተመለሰ፡፡ የኢፌንድያ ልጅ ሰዒድ እንደሚለው እናትዬው ከዚያ በኋላ የነበረውን ጉዞ በእግር ለማድረግ ተገደዋል፡፡ ይህ ደግሞ በዕድሜ ለገፉት እናት ፈታኝ ነበር፡፡

ሰዒድ ለመጨረሻ ጊዜ በቪድዮ ስናወራ ፊቷ ላይ ከፍታ ድካም ይስተዋል ነበር ብሏል፡፡ ልጅዬው ከመጨረሻው የቪድዮ ቆይታ በኋላ እናቱን ዳግም ለማየት አልታደለም፡፡ አዛውንቷ እናት አፌንዲያ ድካማቸው የሚያባራ ስላልሆነ በዚያው ከዚህ ዓለም ሕይወት ተለዩ፡፡

የሕይወት ዘመን ምኛታቸውን ለመሙላት ወደ መካ በደላላ ያቀኑት የእናት ኢፌንዲያ መለየት ልጆቹን ከፍተኛ ሐዘን ውስጥ ጥሏል፡፡ የአዛውንቷ የመጨረሻ ልጅ መናል “ያለ እናቴ መኖር ያስፈራኛል” ብላለች – ለመገናኛ ብዙኃን፡፡ ሆኖም ጥቂትም ቢሆን የሚያጽናናት ነገር ሳይኖር አይቀርም፡፡ እናት በሕይወት ሳሉ፤ “ነቢ (ሰ.ዐ.ወ) ሀገር ሄጄ ሞቼ ብቀበር” ብለው ይመኙ ነበር፡፡

የግብጻዊቷ እናትና ሌሎች ምዕመናን በሐጅ ሥነ ሥርዓት ላይ እያሉ በፀሓይ ንዳድ ተመትተው የመሞት ዜና የዓለም መገናኛ ብዙኃን ርእስ ሆኗል፡፡ እስከ ዛሬ ማለዳ ድረስ በወጡ መረጃዎች የሟቾች አሐዝ 1 ሺሕ 81 ደርሷል፡፡ ነገር ግን ይህ ቁጥር በሳዑዲ ዐረቢያ ባለሥልጣናት ማረጋገጫ አልተሰጠበትም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular