እሑድ , محرم 8, 1446
Google search engine
Homeዜናና ወቅታዊዜናኪርጊዝስታን የሐላል ኢንዱስትሪ የሚመራበትን አዲስ ሕግ አፀደቀች

ኪርጊዝስታን የሐላል ኢንዱስትሪ የሚመራበትን አዲስ ሕግ አፀደቀች

በማዕከላዊ እስያ ውስጥ የምትገኘው ኪርጊዝስታን፣ የሐላል ኢንዱስትሪ የሚመራበትን ሕግ ማፅደቋን አስታወቀች። አዲሱ ሕግ ለሀገሪቱ አምራች እና የወጪ ንግድ ዘርፍ ሐላል ሥርዓት የሚዘረጋ ነው ተብሏል።

በሀገሪቱ ፓርላማ የተዘጋጀው የሕግ ረቂቅ፣ የፕሬዝዳንት ሳዲር ያፓሮቭ ፊርማ አርፎበት መፅደቁን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ያመለክታል።

የአዲሱ ሕግ መውጣት በዘርፎቹ ሥርዓት እንዲሰፍን ከማድረጉ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ መሥፈርቶችን በማሟላት ለአምራች እና ምርቶች ተዓማኒነት የሚፈጥር መሆኑም ተገልጿል። ለሐላል ኢንዱስትሪ የወጣው ሕግ ከአምራቾች ጎን ለጎን የምርት ተጠቃሚዎችን መብት የሚያስጠብቅ ስለመሆኑም ተጠቅሷል።

የሐላል ኢንዱስትሪ የሚመራበትን ሕግ ያወጣችው ኪርጊዝስታን፣ እ.አ.አ ከ2018 አንስቶ ለሐላል ኢንዱስትሪ የሕግ ማዕቀፍ ለማበጀት ሕዝባዊ መድረኮችን በማዘጋጀት ለውይይት ክፍት አድርጋ ነበር።

ኪርኪዝ ሪፐብሊክ የሕዝቧ ብዛት ወደ ሰባት ሚሊዮን ገደማ ይገመታል። ከአጠቃላይ የሕዝብ ቁጥሯ የሙስሊም ዜጎቿ ብዛት ወደ 90 በመቶ የሚደርሰው ኪርጊዝስታን፣ አዲስ ያወጣችውን ሐላል ኢንዱስትሪ የሚመራበትን ሕግ በቀጣይ ወራት ውስጥ ሥራ ላይ ታውለዋለች ተብሎ ተጠብቋል።

ሐላል ኢንዱስትሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ የሚገኝ ነው። ሰባት ዘርፎችን የሚያቅፈው ይህ ኢንዱስትሪ፤ በሥሩ ምግብን ጨምሮ እስላማዊ ፋይናንስ፣ ሐላል ምግብ፣ ሐላል ፋሽን፣ ሐላል ሚዲያ እና መዝናኛ፣ የመድኃኒት እና ሐላል መዋቢያዎችን ያካትታል።

በፍጥነት እያደገ መሆኑ የሚነገርለት ዓለም አቀፉ የሐላል ገበያ፣ 2.3 ትሪሊዮን ዶላር ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ሲሆን እ.አ.አ በ2025 2.5 ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

በኢትዮጵያ በሐላል ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለምርቶች የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሐላል ሠርተፍኬት እንደሚሰጥ ቢናገርም፣ ዘርፉ የሚመራበት ሀገር አቀፍ ሕግ እስካሁን ድረስ አልወጣም። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Google search engine

Most Popular

Recent Comments