የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ በአዲስ አበባ የአከራይና ተከራይ ውል የሚፈጽሙበት ቀን ላይ ገደብ አስቀመጠ። ቢሮው ውል የማይፈጽሙ አከራዮች ቅጣት ይጠብቃቸዋል ሲል አሳስቧል።
የከተማው ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ በ11 ክፍለ ከተሞች እና በ120 ወረዳዎች ውስጥ የአከራይ ተከራይ የውል ስምምነት ከሰኔ 1/2016 ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል።
ውሉ ለሁለት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን የገለጹት ኃላፊዋ፣ በተቀመጠው ጊዜ አከራዮች ተከራይ ማስወጣትም ሆነ የቤት ኪራይ መጨመር አይችሉም ብለዋል።
ምዝገባው እስከ ሰኔ 30/2016 ይቀጥላል የተባለ ሲሆን፣ በተሰጠው ጊዜ ሳይመዘገብ እስከ ሦስት ወራት የቆየ አከራይ የሁለት ወር ኪራይ እንዲሁም ከሦስት ወራት በላይ ካለፈ የሦስት ወር የቤት ኪራይ ቅጣት እንደሚቀጣ በኃላፊዋ መግለጫ ተጠቅሷል።
ወይዘሮ ቅድስት አዋጁ ከፀደቀበት ጊዜ አንስቶ የሚደረግ ማንኛውም የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ የማይፈቀድ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ የመንግሥት ተቆጣጣሪ አካል በሚወስነው መሠረት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ እንዲተገበር የሚያደርገውን አዋጅ ያፀደቀው መጋቢት 24/2016 ነበር።
አዋጁ የቤት ኪራይ የክፍያ ሥርዓት “በባንክ ወይም በሌላ ሕጋዊ በሆነ የኤሌክትሮኒክ ዘዴ ብቻ” እንዲፈጸም የሚያስገድድ ነው።












