እሑድ , محرم 8, 1446
Google search engine
Homeዜናና ወቅታዊዜናበሽግግር ፍትሕ ዙርያ ያጠነጠነ የፖሊሲ ውይይት መድረክ ተከናወነ

በሽግግር ፍትሕ ዙርያ ያጠነጠነ የፖሊሲ ውይይት መድረክ ተከናወነ

እስላማዊ የምርምር እና የባሕል ማዕከል (Islamic Research and Cultural Center – IRCC) ባዘጋጀው የፖሊሲ ውይይት መድረክ በሽግግር ፍትሕ ዙርያ ያጠነጠነ የፖሊሲ ውይይት ተከናወነ። በፖሊሲ መድረኩ ላይ ከተለያዩ ዘርፍ የተውጣጡ ሙስሊም ምሑራን ተሳታፊ ሆነዋል።

ማዕከሉ ዛሬ ቅዳሜ ሰኔ 15/2016 ባዘጋጀው የፖሊሲ ውይይት መድረክ ላይ ውይይት የተካሔደበት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው በሚያዝያ ወር ላይ ነበር።

የዛሬውን መድረክ ያሰናዳው የእስላማዊ ምርምር እና የባሕል ማዕከል፣ በፖሊሲው ላይ ውይይት ያከናወነው በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ላይ የተፈፀሙ ታሪካዊና የቅርብ ጊዜ የመብት ጥሰቶች በሽግግር ፍትሕ ሒደት “ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኙ አስፈላጊ ርምጃዎችን ግልጽ ለማድረግ” በሚል ዓላማ መሆኑን አስታውቋል።

ማዕከሉ መድረኩን ሲያዘጋጅ ካስቀመጠው ዋንኛ ዓላማ ጎን ለጎን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀው ፖሊሲ የታሰበለትን ዓላማ ከግብ እንዲያደርስ የተደረገ መሆኑንም የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ሙሐመድ ዓሊ ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ “ፍሬያማ” ነበር ያሉት የውይይት መድረክ ሙሉ ቀን የተካሄደ መሆኑን በመግለፅ፣ የሚመለከታቸው ምሑራንም መሳተፋቸውን ጠቁመዋል። ከምሑራኑ ጋር በተከናወነው ውይይት በርከት ያሉ ሐሳቦች መነሳታቸውን ያመለከቱት አቶ ሙሐመድ፣ በውይይቱ የዳበሩ ሐሳቦችን ማዕከሉ ካደራጀ በኋላ ሊያደርግ አስቧል ያሉትን ጉዳይ አብራርተዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ከሆነ የእስላማዊ ምርምር እና የባሕል ማዕከል በቀጣይ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በሽግግር ፍትሕ ሒደት ውስጥ ሊያከናውናቸው የሚገቡ ተግባራት እና ተሳትፎን የሚገልፅ ፍኖተ ካርታ የማዘጋጀት ዓላማ አስቀምጧል።

በእስላማዊ ምርምር እና ባሕል ማዕከል ውይይት የተካሄደበት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ፣ ከአስር ቀናት በፊት በፍትሕ ሚኒስቴር የትግበራ ፍኖተ ካርታ እንደተዘጋጀለት የተነገረለት ነው።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዳስታወቀው፣ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ፍኖተ ካርታን ጨምሮ የተዘጋጁ የፖሊሲ ትግበራ ሰነዶች ላይ የሚደረገው ውይይት ሲጠናቀቅ፣ የፖሊሲው ትግበራ ዋና ዋና ተግባራት መከናወን ይጀምራሉ።

በኢትዮጵያ ይተገበራል የተባለው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ውስብስብ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በወንጀል ተጠያቂነት፣ በእውነትን ማፈላለግ፣ ይፋ ማውጣት እና እርቅ ማውረድ፣ በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ምሕረት፣ በተቋማዊ ማሻሻያ እንዲሁም በማካካሻ ሥልቶች የተዋቀረ መሆኑ ተገልጿል።

የዛሬው የፖሊሲ መድረክ ያሰናዳው እስላማዊ የምርምርና የባሕል ማዕከል፣ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ የሚመለከቱ ከ300 በላይ ጥናቶችን የሠራ ሀገር በቀል ድርጅት ነው።

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Google search engine

Most Popular

Recent Comments