ሳዑዲ ዐረቢያ በዘንድሮው ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዓት ለመከወን ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ምዕመናንን አስተናግዳ ወደመጡበት መሸኘት ጀምራለች። በምዕመናን ዘንድ የዕድሜ ዘመን ናፍቆት ለሆነው የሐጅ ክንውን የተቀመጡ ቀናት አልፈው ምዕመናን ወደመጡበት መመለስ የጀመሩት ዛሬ ሐሙስ ነው።

የሳዑዲ ባለሥልጣናት ምዕመናን መካን መልቀቅ መጀመራቸውን ይፋ ሲያደርጉ፣ ጎን ጎን እየወጣ የሚገኘው ዜና አጣብቂኝ ውስጥ የከተታቸው ይመስላል። ዜናው የሞት ነው፤ በፀሓይ ንዳድ ከምድር ሕይወት የተለዩ ምዕመናን ሞት።
በተለይ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ሲከወን እምብዛም ሽፋን በመስጠት በማይታወቁ ምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃን እየተንሸራሸረ የሚገኘው ዜና፣ በሐጅ ሥነ ሥርዐት ወቅት በሳምንቱ መጀመሪያ ከሃምሳ ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ የተመዘገበው ሙቀት ያስከተለው የጤና መቃወስ ቢያንስ የአንድ ሺሕ ምዕመናን ሕይወት ነጥቋል የሚል ነው።
መረጃው ከሲኤንኤን እስከ ሲቢኤስ፤ ከአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እስከ ሬውተርስ እየተዘዋወረ ይገኛል። ማክሰኞ እለት ቀድሞ 550 ምዕመናን ሞተዋል ያለው የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ ዛሬ ሐሙስ የሟቾቹን አሐዝ 1 ሺሕ 81 አድርሶታል። የዜና ወኪሉ ከሟቾቹ ውስጥ ከፍተኛው ቁጥር የግብጻዊያን ነው ያለ ሲሆን፣ የተመዘገበው ቁጥር 658 ነው።
ከእነዚህ ውስጥ 630 ምዕመናን በሐጅ ክንውኑ ላይ ሲሳተፉ የነበረው ለሥነ ሥርዐቱ በተዘጋጀው ቪዛ ሳይሆን በሌላ ዐይነት ቪዛ ቅድስቲቱ መካ ከተማ ተገኝተው ነው። የዜና ወኪሉ በሳዑዲ ባለሥልጣናት ሕገ ወጥ በሚል የተለዩት እነዚህ ምዕመናን፣ ከፖሊስ ለመደበቅ በሚያደርጉት ጥረት የአየር ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው ሥፍራዎች መግባት ስለማይችሉ ለፀሓይ ንዳድ ተጋላጭ ሆነዋል ሲል ለኅልፈታቸው ሰበብ መላ ምት አስቀምጧል።
አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው፣ እስካሁን የሞቱት ከአንድ ሺሕ በላይ ምዕመናን ከአስር ሀገራት የተውጣጡ መሆናቸውን ዲፕሎማቶች እንደነገሩት ነው የጠቀሰው። የዜና ወኪሉ ይህን ቢልም ምዕመናን ራሳቸውን ከፀሓይ ንዳድ ለመከላከል አዘውትረው ዣንጥላ እንዲጠቀሙ ሲመክሩ የቆዩ የሳዑዲ ዐረቢያ ባለሥልጣናት የየትኛውም ሀገር ዜጋ ስለመሞቱ ማረጋገጫ ሲሰጡ አልታዩም።
ሬውተርስ የዜና ወኪል በአንፃሩ አንድ የሳዑዲ ጤና ሚኒስቴር ኃላፊ ሰኞ እለት በምዕመናን ላይ እስካሁን ድረስ ከሌላ ጊዜው የተለየ የሞት ምጣኔ እንዳልተመዘገበ ነግረውኛል ብሎ ዘግቦ ነበር። ኃላፊው የሳዑዲ ጤና ባለሞያዎች በፀሓይ ንዳድ ለተመቱ 2 ሺሕ 700 ምዕመናን የሕክምና ድጋፍ መስጠታቸውን እንደገለፁም አስፍሯል።
የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃን የሑጃጅን የሞት ዜና ሲሸፍኑ በዋሉበት ዛሬ ሐሙስ፣ 12 ሺሕ ምዕመናንን የላከው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በተቃራኒው ለሐጅ ክንውን ከተጓዙ ኢትዮጵያውያን ውስጥ በፀሓዩ ንዳድ ሳቢያ ሕይወቱ ያለፈ ምዕመን አለመኖሩን አስታውቋል፡፡ ምክር ቤቱ በንዳዱ የሞተ እንደሌለ ቢጠቅስም አምስት ኢትዮጵያውያን በሌላ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን ግን በመረጃው አሥፍሯል፡፡ ከምዕመናኑ መካከል አንደኛው የሞቱት በተሽከርካሪ አደጋ መሆኑን የገለፀው ምክር ቤቱ፣ ለቀሪዎቹ የሞት መንስዔ ብሎ የጠቀሰው ሕመም ነው። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሟቾቹ ኢትዮጵያውያን ሕመም ድንገተኛ ይሁን አልያም ቀድሞ የተለየ የጠቀሰው ነገር የለም። (ሚንበር ቲቪ)












