Homeዜናና ወቅታዊዜናለሐጅ ክንውን ከተጓዙ ኢትዮጵያውያን ውስጥ በሙቀት ሳቢያ ሕይወቱ ያለፈ ምዕመን የለም ተባለ

ለሐጅ ክንውን ከተጓዙ ኢትዮጵያውያን ውስጥ በሙቀት ሳቢያ ሕይወቱ ያለፈ ምዕመን የለም ተባለ

ከሙቀቱ ውጪ የአምስት ምዕመናን ሕይወት ማለፉን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤቱ አስታውቋል

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለሐጅ ክንውን ከተጓዙ ኢትዮጵያውያን ውስጥ በሙቀት ሳቢያ ሕይወቱ ያለፈ ምዕመን አለመኖሩን አስታወቀ፡፡ ምክር ቤቱ በሙቀቱ የሞተ ባይኖርም ሁለት ኢትዮጵያውያን ምዕመናን ሕይወታቸው አልፏል ብሏል፡፡

ኢትዮጵያ ለዘንድሮው ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ከላከቻቸው 12 ሺሕ ምዕመናን ውስጥ በሙቀት የሞተ ባይኖርም በሌላ ምክንያት አምስት ሞት መመዝገቡን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮ ጠቅላይ ምክር ቤት ያስታወቀው ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 13/2016 ባወጣው መረጃ ነው፡፡

ምክር ቤቱ በሐጅ ጉዞ ወቅት የነበረው ሙቀት በጣም ከፍተኛ መሆኑን ቢያስታውስም፣ ለሐጅ ተግባር ከመጡ ኢትዮጵያውያን ውስጥ በሙቀቱ ሳቢያ የተጎዳ አለመኖሩን በመጠቆም፣ አምስት ምዕመናን ሕይወታቸው ያለፈበትን ምክንያት አስቀምጧል፡፡ ማንነታቸው ካልተገለጸው አምስት ምዕመናን አንደኛው በመኪና አደጋ እንዲሁም ቀሪዎቹ በሕመም ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን ገልጧል፡፡ ምክር ቤቱ በመኪና አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው ምዕመን “አባት” መሆናቸውን ጠቅሷል፡፡

ለ1445 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዓት ከመላው ዓለም ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሑጃጅ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ አምርተው ክንውኑ መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡ በሥነ ሥርዐት ላይ ለተሳተፉ ሑጃጅ ፈተና ሆኗል በሚል በሳዑዲ ዐረቢያ ቅድስት ከተሞች የተመዘገበው ከፍተኛ መጠን ያለው ሙቀት ሲጠቀስ ነበር፡፡

የፈረንሳዩ ዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዐረብ ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በክንውኑ ወቅቱ በተዘገበው ከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ 550 ምዕመናን ሞተዋል፡፡  አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ከዲፕሎማቶች ሰምቻለሁ ያለው መረጃ እስካሁን ድረስ በሳዑዲ ዐረቢያ ባለሥልጣናት ማረጋገጫ አልተሰጠበትም፡፡ የዜና ወኪሉ ይፋ ባደረገው አሐዝ መሠረት በርካታ ምዕመናን የሞቱባት ግብጽ ነች፡፡ ግብጽ የሞቱባት ሑጃጅ ቁጥር 323 ነው፡፡

ከግብጻዊያኑ በተጨማሪ 35 ቱኒዝዊያን፣ 44 የኢንዶኔዠየያ ዜጎች እና 11 ኢራናውያን ሕይወታቸው ማለፉ ሲገለጽ፣ የዮርዳኖስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ41 ዜጎቹን ሥርዐት ቀብር ለመፈጸም ፍቃድ እንደተጠየቀ አስታውቋል፡፡ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሞቾቹ ውስጥ ስድስቱ በሙቀት ምክንያት መሆኑን ገልጧል፡፡

የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዛሬ ባወጣው መረጃ የ1445 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን መጠናቀቁን በመግለጽ፣ ሥርዓቱ ስለተጠናቀቀ ‘ጠዋፈል ኢፋዷህ’ አድርገው የጨረሱ ምዕመናን እንደ አመጣጣቸው ተራ ወደ ሀገር ቤት እንደሚመለሱ ነው የገለጸው፡፡ ምክር በቤቱ ወደ ሚና ተጉዘው የነበሩ ሐጃጆች ትናንት ረቡዕ አመሻሽ ተጠናቅቀው መካ ከተማ ገብተዋል ብሏል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular