ዒድን በፀጥታ

የ78 ዓመቱ አዛውንት ማላን ከቢሩ ቱዱን ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታዋ መላ ቅጡ በጠፋበት ናይጄሪያ ውስጥ ነዋሪ ናቸው። ማላን ከትናንት አንስቶ እየተከበረ የሚገኘውን የዒድ አል አድሃ በዓል እንደወትሮው የሚደረገውን በማድረግ እያከበሩ አይደለም። በፀጥታ ውስጥ እያሳለፉት ነው።

አዛውንቱ ከዚህ ቀደም እንዳስለመዱት የታዘዙትን ለመፈፀም ለመሥዋዕትነት ያዘጋጁት ነገር የለም። ሌላ እንደሚሆነው ያረዱትን በግ፣ በሬ አልያም ግመል ከቤተሰብና ጎረቤት ጋር አልተቋደሱም። ይህ የሆነው በፍቃዳቸው አይደለም። የወቅቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ አልቀመስ ብሎ ነው። ከቢሩ ለሃምሳ ዓመታት ሲፈፅሙት የኖሩት ዘንድሮ ከብዷቸዋል።

ሙስሊሞች በብዛት በሚኖሩበት የናይጄሪያዋ ሰሜናዊ ግዛት ካኖ፣ አንዳንዶች በእኛ ሀገር የተለመደውን ቅርጫ በመግባት ሥርዐቱን ቢያሳልፉም፣ እንደ አዛውንቱ ከቢሩ ያሉ ምዕመናን ደግሞ ዒድ አል አድሃን በፀጥታ እያሳለፉ ነው።

ከእነዚህ ውስጥ የሆነው የ54 ዓመቱ ሸምሱ ሙሐመድ፣ ለዒድ የመሥዋዕት በግ ለመግዛት ከሰው ገንዘብ ቢያገኝም፣ በግ ከመግዛት ይልቅ የወር አስቤዛዬን መሸመት መርጫለሁ ይላል። ሸምሱ ይህን ማድረግ የመረጠው ለምን እልንደሆነ ሲያብራራ፤ እስልምና የዒድ አል አድሓ እርድን ግዳጅ ያደረገው አቅማቸው ለሚችል መሆኑንም ያስታውሳል።

ኢኮኖሚው ምዕመናንን ሲደቁስ፣ እንደ በግ ነጋዴው ኢብራሂም ባላራቤ ያሉ ዜጎችም ነግደው ማትረፍ ሩቅ ሆኖባቸዋል። ኢብራሂም ለዘንድሮው የዒድ አል አድሓ በዓል የሸጥኩት ሰባት በግ ብቻ ነው ብሏል – ለጋዜጠኞች።

በናይጄሪያ በአሁኑ ሰዓት አንድ መካከለኛ በግ በ100 ሺሕ ናይራ (63 ዶላር) እየተሸጠ ይገኛል። በሀገሪቱ የምግብ ዋጋ ግሽበት 50 በመቶ ደርሷል። ናይጄሪያ እያስተናገደች የምትገኘው የኑሮ ውድነት በሠላሳ ዓመት ውስጥ ተመዝግቦ የሚያውቅ እንዳልሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

የሀገሪቱ መንግሥት ኑሮ ይበልጥ ለበረታባቸው 15 ሚሊዮን ዜጎች ወርሐዊ 16 ዶላር ተቆራጭ ቢያደርግም መቆጣጠር የቻለ አይመስልም። የሀገሬውን ኢኮኖሚ የሚከታተሉ ተንታኞች ኑሮ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ የሕዝቡ ቁጣ ገንፍሎ ሀገሪቱ ወደ ቀውስ ልታመራ ትችላለች ሲሉ ሥጋታቸውን ያጋራሉ። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular