Homeዜናና ወቅታዊዜናከአምስት መቶ በላይ ሑጃጅ ሕይወቱ አልፏል ተባለ

ከአምስት መቶ በላይ ሑጃጅ ሕይወቱ አልፏል ተባለ

የኢትዮያውያን ሞት ከተመዘገበ ይፋ የሚደረገው ሑጃጅ ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ መሆኑ ታውቋል

በዘንድሮው ዓመት ለሐጅ ሥነ ሥርዓት ክንውን ወደ መካ ካመሩ ሑጃጅ መካከል ከአምስት መቶ በላይ ምዕመናን ሕይወታቸው ማለፉ ተነገረ፡፡ ከሟቾቹ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ግብጻዊያን ናቸው ተብሏል፡፡

ለ1445 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዓት ከመላው ዓለም ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሑጃጅ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ አምርተው ክንውኑ መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡ በሥነ ሥርዐት ላይ ለተሳተፉ ሑጃጅ ፈተና ሆኗል በሚል በሳዑዲ ዐረቢያ ቅድስት ከተሞች የተመዘገበው ከፍተኛ መጠን ያለው ሙቀት ሲጠቀስ ነበር፡፡

የፈረንሳዩ ዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዐረብ ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በክንውኑ ወቅቱ በተዘገበው ከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ 550 ምዕመናን ሞተዋል፡፡ የሳዑዲ ዐረቢያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ባወጣው መረጃ ሰኞ ሰኔ 10/2016 ከእስካሁኑ በመጠን ከፍተኛ የተባለው 51.8 ዲግሪ ሴልሽየስ ሙቀት ተመዝግቧል፡፡

የዜና ወኪሉ ይፋ ባደረገው አሐዝ መሠረት በርካታ ምዕመናን የሞቱባት ግብጽ ነች፡፡ ግብጽ የሞቱባት ሑጃጅ ቁጥር 323 ነው፡፡ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ከዲፕሎማቶች ሰምቻለሁ ያለው መረጃ እስካሁን ድረስ በሳዑዲ ዐረቢያ ባለሥልጣናት ማረጋገጫ አልተሰጠበትም፡፡

ከግብጻዊያኑ በተጨማሪ 35 ቱኒዝዊያን፣ 44 የኢንዶኔዠየያ ዜጎች እና 11 ኢራናውያን ሕይወታቸው ማለፉ ሲገለጽ፣ የዮርዳኖስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ41 ዜጎቹን ሥርዐት ቀብር ለመፈጸም ፍቃድ እንደተጠየቀ አስታውቋል፡፡ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሞቾቹ ውስጥ ስድስቱ በሙቀት ምክንያት መሆኑን ገልጧል፡፡

ሚንበር ቲቪ ከሟቾቹ መካከል ኢትዮጵያውያን ሑጃጅ መኖራቸውን ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን ቢጠይቅም፣ ሕይወታቸው ያለፈ ካሉም ይፋ የሚደረገው ሑጃጅ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ መሆኑን ሰምቷል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው የሐጅ ሥነ ሥርዓት ተመክሮ ለሑጃጅ ሞት መንስዔ ተደርጎ ይቀርብ ለማረፊያነት የተዘጋጁ ድንኳኖች በሑጃጅ ላይ መውደቅ እንዲሁም በግፊያ መሃል የሚኖረው መረጋገጥ ነበር፡፡

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular