ይህን የተናገረው ኸሊፋ አል ሐማዲ የተባለ ምዕመን ነው። ኸሊፋ ዘንድሮ ለሐጅ ክንውን ከታደሉ ሙስሊሞች ውስጥ አንዱ ነው።
ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የተነሳው ኸሊፋ፣ የዘ ናሽናል ኒውስ ጋዜጠኛ ሲያገኘው፣ የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙኃን ሳዑዲ ለሐጅ የተጓዙ ሙስሊሞች ‘‘በፀሐይ ንዳድ ከሰሉ” የሚለውን ሟርት መሣይ ዘገባ ዳግም ለማስተጋት ይመስል ነበር። በሐጅ ሥነ ሥርዓት ላይ ጊዜውን ያሳለፈው ኸሊፋ ግን በጋዜጠኛው ይህን ጥያቄ ዳግም ቢጠየቅም የፀሓዩ ንዳድም ሆነ ወሬው ግድ የሚሰጠው አልሆነም።
ኸሊፋ በአንጻሩ የሐጅ ቆይታው በመንፈሥ ከፍ ያለበት እንደሆነ ይናገራል። ሥሜቱን ሲጠየቅ፦ ‘‘እስከዛሬ የኖርነው እዚህ የመንፈሥ ከፍታ ላይ ለመድረስ ይመስላል” ይላል። አንድ ሰው እዚያ ቦታ ላይ ተገኝቶ ሊያደርግ የሚችለው ብቸኛ ነገር አላህ ምሕረትን እንዲለግሠው ዱዓ ማድረግ መሆኑንም ይገልጻል።
የበረሐማዋ ሳዑዲ ዐረቢያ የወቅቱ የአየር ጠባይ ሙቀቱ የበረታበት ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህ ሰበብ ምዕመናን ላይ ጉዳት ሊከሰት ይችላል በሚል ሥጋት ቢኖርም እስከዛሬው እለት ድረስ ከሌላ ጊዜው የተለየ ችግር ስለመፈጠሩ በይፋ የተነገረ ነገር የለም። በርግጥ ለሐጅ ክንውን ብዙም ሽፋን ሲሰጥ የማይታየው ሲኤኤንን አምስት ሑጃጅ በልብ ድካም ሞቱ የሚል ዘገባ ዛሬ እሑድ ማጋራቱ አልቀረም። የጣቢያው ዘገባ በሳዑዲ ዐረቢያ ባለሥልጣናት ይፋዊ ማረጋገጫ አልተሰጠበትም።
በዘንድሮ የሐጅ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመሳተፍ የታደሉ ምዕመናን፣ መካ እና ዙሪያ ገባውን በማካለል ዋንኛቹን የሐጅ ክንውኖች እያጠናቀቁ ይገኛሉ። ትናንት ከፍ ካሉበት ዓረፋ ተራራ ወደ ሙዝደሊፋ ተጉዘው ለድጋሚ ጠዋፍ ወደ አላህ ቤት ደርሰዋል።
የሳዑዲ ዐረቢያ የስታትስቲክስ ባለሥልጣን መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በሐጅ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተሳተፉ ምዕመናን ይፋዋ አሐዝ 1 ሚሊዮን 833 ሺሕ 164 ነው። ከእነዚህ ምዕመናን መካከል 1 ሚሊዮን 611 ሺሕ 310 ምዕመናን ከሳዑዲ ውጭ ከሌሎች ዓለማት የመጡ ናቸው። ቀሪዎቹ እዚያው ሳዑዲ ውስጥ ነዋሪዎች መሆናቸው ተገልጿል። በሥር ሥርዓቱ ላይ 958 ሺሕ 137 ወንዶች ሲሆኑ፣ 875 ሺሕ 27 ሴቶች ናቸው። (ሚንበር ቲቪ)












