የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፣ በዛሬው እለት በከተማዋ በሚገኘው ስታዲየም የተከናወነው የዒድ ሰላት ቀድሞ ከተጠቀሰው ሰዓት አስቀድሞ መከናወኑን አስታወቀ። የከተማው እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፣ ወደ ስታዲየም አምርተው ሰላት ላመለጣቸው ምዕመናን ይቅርታ ጠይቋል።
የከተማው እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዛሬ ከእኩለ ቀን በኋላ እንዳለው ከሆነ፣ የዒድ ሰላት ቀድሞ ከተያዘለት ሰዓት አስቀድሞ የተከናወነው ‘‘የሚያስገድድ ምክንያት” ስለገጠመኝ ነው ብሏል። ምክር ቤት በመግለጫው ለሰላት ሰዓት ለውጥ አስገዳጅ ያለውን ምክንያት አልጠቀሰም።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፣ ትናንት ቅዳሜ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፣ የዒድ ሰላት በስታዲየም የሚሰገደው ጧት 2:30 እንደሚሆን አስታውቆ ነበር።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባወጣው መረጃ ሰዓቱን በመቀየር 2 ሰዓት ላይ እንዲጀመር ማሳወቁን ቢገልፅም፣ የሰዓት ለውጡ ማኅበረሰቡ ከተጠራበት ሰዓት በጣም የቀደመ ስለሚሆን ቢያንስ 2:15 እንዲሰገድ እንደተወሰነ ገልጿል።
የ1445 ዓ.ሂ የዒድ አል አድሓ በዓል ዛሬ እሑድ በመላው ዓለም ምዕመናን ዘንድ እየተከበረ ይገኛል። በዓሉ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ማለዳ ላይ በሰላት ተጀምሯል።












