አሕመድ ሑሴን (አቡ ቢላል) በበርካታ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ቤት የመጻሕፍት መደርደሪያ ላይ ተደጋግሞ የሚታይ የደራሲ ሥም ነው። በአማርኛ ቋንቋ ለአንባቢያን በቀረቡ እስላማዊ ይዘት ባላቸው መጻሕፍት ዝግጅት ድርሻው ቢሠፈር ከፍተኛውን ከሚወስዱት ውስጥ ከፊት የሚሠለፍም ነው። ከስልሣ በላይ መጻሕፍት በሥሙ የሚጠሩለት አሕመድ ሑሴን፣ አንባቢዎቹን እንዳስለመደው በቅርብ ሳምንታት ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ይዞ ሊቀርብ መሰናዶውን አጠናቋል። አሕመድ ሑሴን (አቡ ቢላል) ስለ አዲሱ መጽሐፉ እና እስላማዊ መጻሕፍት ዝግጅት ከሚንበር ቲቪ ድረ ገጽ ጋር አጭር ቃለ ምልልስ አድርጓል። መልካም ቆይታ፦
ሚንበር ቲቪ፡- ጥቂት ስለ አዲሱ መጽሐፍ ንገረን፤ ምን ያህል ጊዜ ፈጀ?
አቡ ቢላል፡- የመጽሐፉ ርእስ “አል—ፋሩቅ ዑመር ቢን አል ኸጣብ” ይሠኛል። የገጽ ብዛቱ እኔ እጅ እስከነበረ ጊዜ ድረስ 843 አካባቢ ነው። ማውጫ፣ የመግቢያ ጽሑፍ (ሙቀዲማ) ወዘተ ሲገባበት ወደ 850 ገጽ መሻገሩ አይቀርም። የፈጀብኝ ጊዜ ወላሂ እያመመኝ በመሃል እያቋረጥኩ ስለምሠራ ከስምንት ወር በላይ ይሆናል። ተተይቦ ሁለት ጊዜ አርሜዋለሁ፤ [ስምንት ወሩ] ከእነእርማቱ የወሰደው ጊዜ ነው። እንደአለመታደል ሆኖ እየተረጎሙ በኮምፒውተር መጻፍ አይመቸኝም፤ አይሳካልኝም። ስለሆነም ተያቢዎቹ እንደነገሩ የሆነውን የእጅ ጽሑፌን መልሰው እየሰጡኝ ነው ለሁለት ጊዜያት ያረምኩት። ከዚያም ወንድማችንና ብርቱው ጸሐፊ ሙሐመድ ሰዒድ (Abx) ለአንድ ዙር ዐይቶታል (አርትዖቱን ሠርቶታል)።
ሚንበር ቲቪ፡- ባለፉት ዓመታት በገጽ ብዛት ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ስታዘጋጅ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። አሁን በድጋሚ የመጣኸው ቀዳሚው መጽሐፍ ከአንባቢ ምላሹ አበረታች በመሆኑ ነው? በቀጣይ ተመሳሳይ መጽሐፍ መድገም በእቅድህ ውስጥ አለ?
አቡ ቢላል፡- ከመጽሐፎቼ ሁሉ ለእኔ ልዩ እና በላጭ የምለው ባለ 936 ገጹ “ለዓለማት እዝነት” የተባለው መፅሐፌን ተርጉሜው የታተመው በ2009 ነበር። አሁን ይኸኛውን መተርጎሜ የቀዳሚው መጽሐፌ ምላሽ (ሰው በማንበብ የሰጠው ግብረ መልስ) መልካም በመሆኑ ላይ ጥገኛ ሆኖ አይደለም። በአጋጣሚ “ለዓለማት እዝነት” በጣም ማራኪና በውስጡ ብዙ ነገሮችን ያካተተ የሲራ ዐውደ ጥበብ (Encyclopedia) በመሆኑ ሰው ይገዛዋል፤ ያነበዋልም ጭምር። ከዩኒቨርስቲ እና ከዲን ኮሌጆች ለሚመረቁ ተማሪዎች ወዳጅ ዘመድ በሥጦታ ያበረክተዋል። ይህን ስል በአንፃራዊነት ነው። ደራሲው ሊቢያዊው ዶ/ር ዐሊ ሙሐመድ አስ ሶልላቢ ከዚህ መጽሐፍ በኋላ በተከታታይ በዚሁ ስልትና የጽሑፍ ይትባሃል (Style) የኹለፋዕ አር ራሺዲንን፣ የሐሰንና ሐሴይን (ረ.ዐ)፣ የሳላህዲን አል አዩቢን ወዘተ ታሪኮች አዘጋጅተዋል።
እንደሚታወቀው በሀገራችን የኸሊፋዎቹን ታሪክ የያዙ በዚህ መጠንና ጥልቀት የተዘጋጁ መጻሕፍት የሉም። ርግጥ ነው አነስተኛ ገጽ ያላቸው፣ ወይም ደግሞ የሁሉንም ኸሊፋዎች ታሪኮች አዳብለው በአንድ ቅፅ የያዙ (ወንድም አቡበከር ዓለሙ የተረጎመውን ማውሳት ይቻላል) ታትመዋል። ግና የሚያጠረቃና አጠቃላይ የኸሊፋዎቹን ዜና መዋዕል የያዘ ሥራ ለትውልድ ማቀበል እንደሚያስፈልግ የእኔም ሆንኩ አሳታሚው ነጃሺ ማተሚያ ቤት እምነት ስለሆነ ተሠራ። ከሁሉም በፊት በነበራቸው ቀዳሚነት የአቡበከር (ረዐ) ታሪክ “አስ ሲዲቅ አቡበከር” ተተርጎሞ ገበያ ላይ ከወጣ ቆየ። ከዚያም “አል ፋሩቅ ዑመር” ተከትሏል። “ዙን ኑረይን ዑስማንን” ተርጉሜ አስተካክዬ ጨርሻለሁ። በአላህ (ሱ.ወ) ፍቃድ አርታዒው ከደባበሰው በኋላ ክረምቱን ቢቀር በመጪው ዓመት መጀመርያ ይታተማል ብዬ አስባለሁ። የ“አል ሃይደር ዐሊ”ን ትርጉም ሩብ ያክል ሄጃለሁ። የአላህ እገዛ ከተገኘና ጤናዬ ከተስተካከለ፤ ቢበዛ ስምንት ወራት ቢፈጅብኝ ነው። የገጽ ብዛቱ ከአል ፋሩቅ ዑመር (ረዐ) ቢበዛ እንጂ አያንስም።
ሚንበር ቲቪ፡- በተደጋጋሚ እንደሚባለው እስላማዊ መጻሕፍት አንባቢ የላቸውም። ጥቂት ቅጂ ታትሞ ተሽጦ ለማለቅ ረዥም ጊዜ ይወስዳል። ይህ የጸሐፊዎችን ተነሳሽነት ማሽመድመዱ አይቀርም። አንተ ይህን ስሜት በምን ታስታርቀዋለህ? መጽናኛህ ምንድን ነው?
አቡ ቢላል፡- ሙስሊሙ በቀደምት ሥርዐቶች እንዳይማርና ከዕውቀት ጋር እንዳይገናኝ ሆኖ ኖሯል። እንደ ኢትዮጵያዊነትም ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር ተጃምሎ ሕዝቡ ማንበብ አይወድም። አሁን ደግሞ በእንቅርት ላይ እንዲሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እያሳደሩ የሚገኙት ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው። በዚህ ሁሉ የተነሳ ሞራላችን ብዙ ጊዜ እንክሽክሽ ይላል። ግና ደግሞ ጨርሰን ተስፋ መቁረጥ ውስጥ አንገባም። ዐየህ! እነዚህን መጻሕፍት ከአምስት መቶ ዓመታት በኋላ አቧራቸውን አራግፎ እያነበበ የሚገረም ትውልድ ሊመጣ ይችላል፤ ማን ያውቃል?! እናም ተተርጉመው ይቀመጡ።
ሚንበር ቲቪ፡- እንደ ሙስሊም የምትጽፈው ለምንድን ነው? ወይም አንድ ሙስሊም ጸሐፊ ምን ላግኝ ብሎ ይጽፋል?
አቡ ቢላል፡- አንድ ታላቅ (ሰለፍ) “በዱኒያ አንዳች ነገር መጨመር የማትችል ከሆንክ አንተ ራስህ ጭማሪ ነህ” የምትል አባባል አለቻቸው። እኔም ጭማሪ ላለመሆን እፍጨረጨራለሁ፤ በአላህ እዝነት። ሲቀጥል ሩሔ ከጽሑፍ ጋር የተሳሰረች በመሆኗ እንዲህ እያመመኝም እንኳን ቢሆን መጻፍ አልተውኩም። የእንጀራ ነገር ቢሆን ወዳጅ ዘመድ አስቸግሬ ሌላ ነገር እሠራ ነበር። ግና ነፍሴ ተራ ሕይወት ገፍታ ለመኖር አልተኸለቀችም። በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ባገኝ እንኳን የምተወው አይመስለኝም። ባይሆን የኸሊፋዎቹን ትርጉም እንደጨረስኩ ወደ ምርምር ሥራዎች ፊቴን ለማዞር አስባለሁ፤ የኻሊቀል ከውኑ ፍቃድ ቢሆን፡፡
ሚንበር ቲቪ፡- ከአዲሱ መጽሐፍ በተጨማሪ በቅርብ ምን እንጠብቅ?
አቡ ቢላል፡- በቀጣይ ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት “ዙን ኑረይን ዑስማን” ይወጣል፡፡ በአላህ ፍቃድ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ሚንበር ቲቪ፡- እናመሰግናለን፡፡












