Homeዜናና ወቅታዊዜናቀለም ፋውንዴሽን በመቐለ ከተማ ሁለገብ የወጣቶች ሥልጠና ማዕከል አስመረቀ

ቀለም ፋውንዴሽን በመቐለ ከተማ ሁለገብ የወጣቶች ሥልጠና ማዕከል አስመረቀ

በዋነኝነት ወጣቶችን ማዕከል አድርጎ የሚሠራው ቀለም ፋውንዴሽን፣ በትግራይ ክልል መቀመጫ መቐለ ከተማ ሁለገብ ሥልጠና ማዕከል አስመረቀ፡፡ ፋውንዴሽኑ ከመቐለ በተጨማሪ በቀጣይ በሌሎች የክልሉ ከተሞች ቅርንጫፍ የመክፈት ዕቅድ መያዙን አስታውቋል፡፡

በተያዘው ዓመት የተቋቋመው ቀለም ፋውንዴሽን፣ መቐለ ከተማ ቤተ መጻሕፍት ያካተተውን የሥልጠና ማዕከሉን ያስመረቀው እሑድ ግንቦት 18/2016 ነው፡፡ በዚህ ሥነ ሥርዐት ላይ ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የሥልጠና ማዕከሉን ያስመረቀው ቀለም ፋውንዴሽን፣ ቤተ መጻሕፍቱን ያካተተው ማዕከል በከተማው ውስጥ ለሚገኙ ታዳጊዎችና ወጣቶች አገልግሎት እንደሚሰጥ የማዕከሉ መሥራች እና ምክትል የቦርድ ኃላፊ የሆኑት አቶ ኢስማኤል ኢድሪስ ለሚንበር ቲቪ ተናግረዋል፡፡ ማዕከሉ ወጣቶች የንባብ ባሕላቸውን የሚያዳብሩበት፣ የትምሕርት እና ሥልጠና አገልግሎት የሚያገኙበት መሆኑንም ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

አቶ ኢስማኤል ኢድሪስ

አቶ ኢስማኤል ማዕከሉ ለወጣቶች ይሰጣቸዋል ካሏቸው ሥልጠናዎች ውስጥ የንግግር ክሕሎት፣ ችግር አፈታት እና የጊዜ አጠቃቀም ይገኙበታል፡፡ ፋውንዴሽኑ ለወጣቶች የማማከር አገልግሎት እንደሚሰጥም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ለሁለት ዙር የወጣቶች ሥልጠና መሰጠቱንም አክለዋል፡፡ አቶ ኢስማኤል የማማከር አገልግሎቱ ያስፈለገው ወጣቶቹ ባለፉት ዓመታት በወረርሽኝ እና ጦርነት ውስጥ በማለፋቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሐጅ መሐመድ ካሕሳይ በመድረኩ ላይ

እንደ አቶ ኢስማኤል ከሆነ ማዕከሉ በዋነኝነት ወጣቶችን ታሳቢ በማድረግ የተቋቋመ ቢሆንም ለሌሎች የኀብረተሰብ ክፍሎችም አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ኃላፊው ቀለም ፋውንዴሽን ወደፊት ለመሥራት በእቅድ ከያዛቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል የንግዱ ማኅበረሰብ እና ወላጆች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡

ቀለም ፋውንዴሽን ከዚህ በተጨማሪም ዘካ በመሰብሰብ በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ተሳታፊ እንደሚሆን ተገልጧል፡፡ ፋውንዴሽኑ ባለፈው ረመዳን ወር መቐለ እና ኮረም ከተሞችን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት ለአቅመ ደካሞች የዐይነት ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ቀለም ፋውንዴሽን በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከመቐለ ከተማ በተጨማሪ በሌሎች የትግራይ ክልል ከተሞች ቅርንጫፉን የማሳዳግ እቅድ መያዙን የማዕከሉ መሥራች እና ምክትል የቦርድ ኃላፊ የሆኑት አቶ ኢስማኤል ኢድሪስ ገልጸዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular