እሑድ , ذو الحجة 17, 1445
Google search engine
Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችመጅሊስ ተቃውሞ ስላቀረበበት የሀገራዊ ምክክር እስካሁን የምናውቃቸው ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?

መጅሊስ ተቃውሞ ስላቀረበበት የሀገራዊ ምክክር እስካሁን የምናውቃቸው ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?

ስለ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ የተቋቋመው በታኅሣሥ ወር 2014 ነበር፡፡ ኮሚሽኑ በአዋጅ ሲቋቋም በኢትዮጵያ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ “ልዩነቶችና አለመግባባቶች” ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ ምክሮችን በማካሄድ፣ ምክረ ሐሳቦችን በማቅረብ እና ለተግባራዊነቱም የመከታተያ ሥርዐት በመዘርጋት ለሀገራዊ መግባባት ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ተልዕኮ በመያዝ ነው፡፡

በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በመለየት እና ውይይቶቹ የሚካሄዱባቸውን ርእሰ ጉዳዮች በመለየት ምክክር እንዲደረግባቸው በማመቻቸት ዓላማ የተቋቋመው ኮሚሽኑ፤ የሚካሄዱት ሀገራዊ ምክክሮች “አካታች፣ ብቃት ባለውና ገለልተኛ በሆነ አካል የሚመሩ፣ የአለመግባባት መንስዔዎችን በትክክል በሚዳስስ አጀንዳ የሚያተኩሩ፣ ግልፅ በሆነ የአሠራር ሥርዓት የሚመሩ እና የምክክሮቹን ውጤቶች ለማስፈፀም የሚያስችል ዕቅድ ያላቸው” እንዲሆኑ በማድረግ ውጤታማ የሆኑ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ተግባራዊ ማድረግንም በተጨማሪነት አንግቧል፡፡

የሚካሄዱትን ሀገራዊ ምክክሮች የሚጠቀመውም በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እንዲሁም በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል፣ መተማመን የሰፈነበትና አዲስ የፖለቲካ ሥርዐት ለመፍጠር በሚያስችል አግባብ ውይይቶቹ እንዲካሄዱ ሥርዓት ለመዘርጋት መሆኑን አሳውቋል፡፡

በዚህ አግባብ የተቋቋመው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ ሥራውን የሚያከናውነው በአራት ምዕራፎች በመከፋፈል ነው፡፡ እነዚህ አራት ምዕራፎች የቅደመ ዝግጅት፣ የዝግጅት፣ የምክክር እና የምክክር ውጤቶችን መተግበሪያ በሚል ዘርዝሯቸዋል፡፡

በአዲስ አበባ የተጀመረው የምክክር ምዕራፍ

ኮሚሽኑ እስካሁን ድረስ በነበረው የሥራ ሒደት ሁለቱን ቀዳሚ ምዕራፎች በመጠናቀቅ ወደ ሦስተኛው መሸጋገሩን ትናንት ረቡዕ ግንቦት 21/2016 ይፋ አድርጓል፡፡ በዋና ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ በአዲስ አበባ ዐድዋ ሙዝየም በተከናወነ ሥነ ሥርዐት ይፋ የተደረገው ይህ ምዕራፍ “የምክክር” ነው፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ ባደረጉት ንግግር በአዲስ አበባ የተጀመረው ምዕራፍ ለቀጣዩና ለመጨረሻው የምክክር ጉባዔ “ቁልፍ ሚና” የሚኖረው ነው ብለውታል፡፡

በመድረኩ ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ 119 ወረዳዎች በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ከ2 ሺሕ በላይ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ተሳታፊዎቹ የተወከሉት፤ ከመንግሥት እና የግል ተቋማት ሠራተኞች፣ መምህራን፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ተፈናቃዮች፣ የተገለሉ ማኅበረሰቦች እና የኅብረተሰብ መሪዎች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የተወካይ ልየታ እንዴት ይከናወናል?

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የመጀመሪያው ደረጃ የአጀንዳ ሀሳቦች ማሰባሰቢያ መድረኮች ላይ የሚሳተፉ ተሳታፊዎቸን የሚወክሉ ሰዎችን የለየው በወረዳ ደረጃ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ከየወረዳው ከተለዩ በቁጥር ከ8 እስከ 10 የሚደርሱ የማኅበረሰብ ክፍሎች (ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ መምህራን እና የማኅበረሰብ መሪዎች፣ የተገለሉ ኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ዕድሮች እና የንግዱ ማኅበረሰብ፣ ዕድሮች)  በየወረዳቸው 50 ተወካዮችን ከመረጡ በኋላ፤ ለልየታ ወደ የዞን ማዕከላት እንደሚልኩ ከዚህ ቀደም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ወደ ዞን ከመጡት የእያንዳንዱ የማኅበረሰብ ክፍል ተወካዮች ውስጥ ሁለት ሰዎች እንደሚመረጡ ያመለከተው ኮሚሽኑ፤ በክልል ደረጃ በሚካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ የሚሳተፉት እነዚህ ሁለት ተወካዮች ይሆናሉ ብሏል፡፡ በክልል ደረጃ የሚሰበሰቡት ተወካዮች፤ በየወከሉት ኅብረተሰብ ክፍል ተከፋፍለው “ኮከስ” ይፈጥራሉ የተባለ ሲሆን ኮከሶቹ የወከላቸውን የኅብረተሰብ ክፍል አጀንዳ ለኮሚሽኑ የሚያቀርቡ ይሆናል፡፡

በአዲስ አበባ የተጀመረው የምክክር ሒደት በከፊል/የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

መጅሊስ ተቃውሞ ያነሳበት የውክልና ጉዳይ

ዋና ኮሚሽነሩ በዝርዝራቸው ባይጠቅሱትም የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮችም በዚህ የከተማ አስተዳደር ምክክር ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በተጀመረው የክልል/የከተማ አስተዳደሮች የምክክር ምዕራፍ የሚሳተፉ ሰባት የሃይማኖት ተቋማት እያንዳንዳቸው ሦስት ተወካዮች ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከሃይማኖት ተቋማቱ ውስጥ የሕዝበ ሙስሊሙ ወካይ ተቋም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ)፣ በእስካሁኑ የምክክር ሒደት ላይ ያለውን ተቃውሞ ሲገልጽ የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምክር ቤቱ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የጻፋቸው የቅሬታ ደብዳቤዎች እንደሚያሳዩት የምክክር ኮሚሽኑ በእስካሁን ሒደቱ ሙስሊሙ “በቁጥሩ ልክ” ውክልና እንዳልተሰጠው በመግለጽ የተወካይ ልየታው በድጋሚ እንዲቃኝም ጠይቋል፡፡ መጅሊስ ሚያዝያ 25/2016 እና ግንቦት 5/2016 በጻፋቸው ደብዳቤዎች ስላነሳው የተወካይ ልየታ ምላሽ እንዳላገኘ ገልጧል፡፡ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ቅሬታ በክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤትም ተስተጋብቷል፡፡

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ግንቦት 12/2016 ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከተው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ ለአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር እና ለክልሉ ሰላምና ደኅንነት ቢሮ በጻፈው ደብዳቤ ላይ፣ የሀገራዊ ምክክር የተሳታፊ ልየታ አሠራር ሳይሻሻል ባለበት የሚቀጥል ከሆነ ለምክክሩ ዕውቅና እንደማይሰጥ አስጠንቅቆ ነበር፡፡ በምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ጀውሐር ሙሐመድ በተጻፈው ደብዳቤ፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በክልሉ ባካሄደው ጉባዔ ላይ ያሳተፈው “የኔ የሚለውን ብቻ” እንደሆነ ተጠቁሟል። የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤትም ማስጠንቀቂያ እስካሁን ድረስ ምላሽ አላገኘም፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከሁለት ሳምንት በፊት በእስላማዊ ጉዳዮች አተኩረው ከሚሠሩ መገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች እና አንቂዎች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ እስካሁን ድረስ በነበረው በዚህ የልየታ ሒደት የሙስሊሞች ውክልና ከ2 በመቶ ያነሰ መሆኑን የሰበሰበውን መረጃ ዋቢ በማድረግ ጠቅሷል፡፡ 

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰኞ ግንቦት 19/2016 በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የምክክር ምዕራፍ በተመለከተ በሰጠው መግለጫ ከእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ስለሚቀርበው ቅሬታ ከመገናኛ ብዙኃን ጥያቄ የቀረበላቸው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ምክክሩ “ማንንም ያገለለ አይሆንም” ከማለት ውጪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ስለ ቅሬታው ባያነሱም ምክር ቤቱ ለምክክር ሒደት የሚቀርቡ የሀገሪቱን ሙስሊሞች አጀንዳዎችን ማቅረቡን ግን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም

መጅሊስ ካቀረባቸው ዘጠኝ አጀንዳዎች ውስጥ “ታሪክና ትርክት” እንዲሁም “ሀገራዊ እና ሕዝባዊ ምልክቶች” በድጋሚ እንዲቃኙ የሚጠይቀው ይገኝበታል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ባቀረብ ባለ ሃያ ገጽ ሰነድ በአጀንዳነት የቀረቡት ዘጠኝ ጉዳዮችን አካቷል፡፡ እነዚህም ታሪክና ትርክት፣ ሀገራዊና ሕዝባዊ ምልክቶች፣ የሲቪል መብቶችና ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል፣ የሕዳጣን (Minority) መብት፣ የኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አባል መሆን፣ የመንግሥትና ሃይማኖት ግንኙነት፣ ለሙስሊም ጠልነት ዕውቅና መስጠት እና ማስተካከል፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራ እንዲሁም አካታች ኢኮኖሚና ፋይናንስ ማስፈን የሚሉት ናቸው።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ ባስጀመረውና ሰባት ቀናት በሚቆየው ምክክር ተሳታፊ የሆኑ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች በቡድን በመከፋፈል በሚያደርጓቸው ምክክሮች ላይ ከሚወያዩባቸው ርእሰ ጉዳዮች መካከል የግጭቶች መነሻ ዋና ዋና ምክንያቶች፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ እና የነበሩ ዋና ዋና ችግሮች እና የችግሮቹ መሠረታዊ መንስኤዎች የሚሉት ተካተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን ድረስ የመጨረሻውን ምዕራፍ የሚያከናውንበትን ጊዜ በይፋ ባያሳውቅም የሦስት ዓመት ሥልጣን ዘመኑ ሳይጠናቀቅ በፊት የማካሄድ ዕቅድ እንዳለው ከሰሞኑ አስታውቋል፡፡ በ2014 አጋማሽ የተቋቋመው ኮሚሽኑ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሥራ ዘመን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊራዘም እንደሚችል በአዋጁ ላይ ሠፍሯል፡፡

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Google search engine

Most Popular

Recent Comments