እስራኤል ከመስከረም መጨረሻ ወዲህ በጋዛ እየፈጸመች በምትገኘው የበቀል ጥቃት በሰማይ ቦምብ እያዘነበች ሕፃናትን ጨምሮ ንጹሐንን እየጨፈጨፈች ትገኛለች፡፡ እስራኤል በዚህ ጥቃት ቢያንስ 35 ሺሕ ፍልስጤማዊያንን ገድላለች፡፡
ይህ በንጹሐን ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት በሰማይ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ በምድር ጭምር የሚካሄድ ነው፡፡ እስራኤል ከዚያን ጊዜ አንስቶ በንጹሐን ላይ የምትሰነዝረው ጥቃት፣ ከመላው ዓለም ስለ ሰብዓዊነት በሚገዳቸው ብርቱ ተቃውሞ የሚቀርብበት ነው፡፡ ተቃውሞው ከአራቱም የዓለም ጫፍ የሚሰማ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜያት እስራኤልን በምትደግፈው አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ የየኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚያሰሙት ተቃውሞ ትኩሳቱ አሁንም ድረስ እንዳልበረደ ይታወቃል፡፡
ተቃውሞው በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም በዘመነኛው የማኅበራዊ ትስስር መድረክ የቀጠለ ነው፡፡ በዚህ መድረክ ለሰብዓዊነት የሚቆሙ ግለሰቦች ድምጻቸውን ሲያሰሙ፣ ጎን ለጎን የእስራኤልን ሰብዓዊነት የጎደለው ጭፍጨፋ የሚያወድስ፣ ምክንያታዊ ለማድረግ የሚሞክር፣ ለጥቃቶች ማስተባበያ እና የተሳሳተ አውድ የሚሰጥ እንዲሁም እውነታውን የሚያዛባ ባላጋራ ይገጥማዋቸዋል፡፡ ይህ ባላጋራ ሰው አይደለም፡፡ ሰው መሣይ የሶፍትዌር ፕሮግራም ነው፡፡ በባለሞያዎች “ቦት” በሚል ሥያሜ ይጠራል፡፡
“ቦት”፤ ጫጩት ሮቦት እንደማለት ነው፡፡ እንደ ሮቦት አካል መሣይ ነገር ባይገጠምለትም፤ እንደ ሮቦት “ለማሰብ” ፕሮግራም ይደረጋል፡፡ ባለሞያዎቹ ቦትን በሁለት ይከፍሉታል፤ ሰናይ እና መጥፎ በማለት፡፡ ሰናይ ቦት እንደ ጥሩ ረዳት የሰው ልጆችን ኑሮ የሚያቀል ሲሆን፣ መጥፎ ቦት ልክ እስራኤል እንደምትልከው በአደባባይ የሚቀጥፍ ነው፡፡
የእስራኤል ቦቶች በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ሲቀጥፉ እንደሚውሉ የደረሱበት ሊባኖሳዊያኑ አጥኚዎች ራልፍ ባይዱን እና ሚሼል ሴማን ናቸው፡፡ ኢንፍሉአንሰርስ (InflueAnswers) የተሰኘ የጥናት እና አማካሪ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ሁለቱ ሊባኖሳዊያን፣ ይህን ያረጋገጡት ከእስራኤል የበቀል ጥቃት መጀመር አንስቶ ባደረጉት ጥናት ነው፡፡
አጥኘዎቹ እንደሚሉት ከሆነ ቀደም ባለው ጊዜ በፍልስጤማዊያኑ ላይ የሚዘንበውን ዘግናኝ ጥቃት የሚቃወሙ በርካቶች አስተያየታቸውን በነጻነት ይሰጡ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ተቃውሞ አልነበረም፡፡ ጥቂት ቆይቶ ግን ነገሩ እየተለወጠ መጣ፡፡ ፍልስጤማዊያኑን የሚደግፉ አስተያየቶች በተጻፉ አምስት እና አስር ደቂቃ እየጠበቁ የሚሰነዘሩ ምላሾች ቁጥራቸው እየበረከተ መጣ፡፡ ራልፍ ባይዱን እና ሚሼል ሴማን እንደሚሉት ይህ ነበር ለጥናቱ መነሻ የሆነው፡፡ አጥኚዎቹ ይፋ ባደረጉት ጥናት እስራኤል ያሰማራችው ቦት አላማው ፍልስጤማዊያንን የሚደግፉ አስተያየት ሰጪዎችን ማደናገር ነው፡፡
የአሜሪካው የሳይበር ሴኩሪቲ ኩባንያ ኢምፐርቫ ይፋ ባደረገው ጥናት መሠረት እ.አ.አ በ2023 መጨረሻ ላይ ኢንተርኔቱን ካጨናነቀው 49 በመቶ የሚጠጋው ቦት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ሰናይ የሚባሉት ቦቶች ቁጥር 15 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ ቀጣፊዎቹ የእስራኤል ዐይነት ቦቶች ሆነው ተመዝግበዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












