Homeዜናና ወቅታዊዜናሦስት የአውሮፓ ሀገራት በቀጣይ ሳምንት ለፍልስጤም ይፋዊ የሀገርነት ዕውቅና ሊሰጡ ነው

ሦስት የአውሮፓ ሀገራት በቀጣይ ሳምንት ለፍልስጤም ይፋዊ የሀገርነት ዕውቅና ሊሰጡ ነው

አውሮፓውያኑ ሀገራት ኖርዌይ፣ አየርላንድ እና ስፔን በይፋ ለፍልስጤም የሀገርነት ዕውቅና ሊሰጡ መሆኑን ያስታወቁት ዛሬ ረቡዕ ነው፡፡ የሀገራቱ ባለሥልጣናት ዕውቅናው በቀጣይ ሳምንት እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

ሀገራቱ ለፍልስጤም የሀገርነት ዕውቅና የሚሰጡት ለመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም መስፈን እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ ከሀገራቱ ውስጥ የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዩናስ ጋህር ፍልስጤም እና እስራኤል ሁለት ሀገር መሆናቸው ለችግሮች መፍትሔ ያመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በጋዛ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን የግድያ እና ጉዳት ሰለባ መሆናቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ያቀረቡት የመፍትሔ አቅጣጫ ለሰላም ዋስትና የሚሆን ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በዛሬው እለት ኖርዌይ ለፍልስጤም የሀገርነት ዕውቅና መስጠቷ ከተሰማ በኋላ በተመሳሳይ ሌላኛዋ የአውሮፓ ሀገር አየርላንድ የኖርዌይን ፈለግ በመከተል ዕውቅና ሰጥታለች፡፡ የአየርላንድ ዕውቅና ይፋ የተደረገው በጠቅላይ ሚኒስትሯ ሳይመን ሐሪስ አማካኝነት ነው፡፡

ሐሪስ ስለ ጉዳዩ በሰጡት መግለጫ፣ ከሀገራቸው በተጨማሪ ቀዳሚዋ ዕውቅና ሰጪ ኖርዌይ እንዲሁም ስፔን ጭምር ለፍልስጤም ዕውቅና መስጠታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የአየርላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር በቀጣይ ሳምንታት ተጨማሪ ሀገራት ውሳኔያችንን ተከትለው ለፍልስጤም የሀገርነት ዕውቅና ይሰጣሉ የሚል እምነት አለን ሲሉ በርግጠኝነት ስሜት ገልጸዋል፡፡ አልጀዚራ እንደዘገበው ከሆነ በቀጣይ ሳምንታት የእነ አየርላንድን መንገድ ይከተላሉ ተብለው የሚጠበቀት ሀገራት ማልታ እና ስሎቬንያ ናቸው፡፡

ለፍልስጤም ዕውቅና በመስጠት በዛሬው ዕለት ሦስተኛ ሀገር የሆነችው ስፔንም በቀጣይ ሳምንት በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል ዕውቅናውን እንደምታጸድቅ ተነግሯል፡፡ የስፔንን አቋም ይፋ ያደረጉት የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ፣ የእስራኤሉ ቤንያሚን ኔታያሁ በፍልስጤም ሀገር መሆን ላይ ይዘውታል ያሉትን የተሳሳተ አቋም በመግለጫቸው ተችተዋል፡፡  

በዛሬው እለት ሦስት አውሮፓውያን ሀገራት ለፍለስጤም የሀገርነት ዕውቅና ልንሰጥ ነው ማለታቸውን ተከትሎ፣ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ አስተያየት ከሰጡት መካከል የፍልስጤም ነጻነት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ሐሰን አል ሸይኽ ውሳኔውን አወድሰውታል፡፡ በተመሳሳይ ሐማስ የሀገራቱን ውሳኔ በመደገፍ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በአንጻሩ በጋዛ ንጹሐን ላይ ጥቃት እየፈጸመች የምትገኘው እስራኤል ውሳኔውን ተቃውማ መግለጫ አውጥታለች፡፡

የፍልስጤምን የሀገርነት ጉዳይ በቀዳሚነት ያወጀው እ.አ.አ የፍልስጤም ነጻነት ድርጅት (ፒኤልኦ) ነበር፡፡  ፒኤልኦ የፍለስጤምን ሀገርነት ሲያውጅ ድንበር ባያሰምርም፣ አል ቁድስ ዋና መዲና እንደምትሆን አስታውቆ ነበር፡፡

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular