Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮች76 ዓመታት ያስቆጠረው መቅሰፍት

76 ዓመታት ያስቆጠረው መቅሰፍት

ጣሪቅ አቡ አዙም ከሚገኝበት ጋዛ ለዓለም ይድረስ ብሎ ዛሬ ማለዳ ባሠራጨው ዘገባ፣ እስራኤል በፍልስጤም ንጹሐን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት በአየር እና በመሬት መቀጠሏን ይገልጻል፡፡ ጋዜጠኛው የአልጀዚራ ባልደረባ ነው፡፡ ጣሪቅ በተለይ ባለፉት ሰባት ወራት እስራኤል በንጹሐን ላይ ቦምብ ስታዘንብ እግር በእግር እየተከተለ ሲዘግብ ቆይቷል፡፡ ሕፃናት እና እናቶችን ጨምሮ ንጹሐን ሲረግፉ ዐይቷል፡፡ ውሎ አዳራቸውን፣ ሕልማቸውንም ጭምር የሚያጋሩት ወዳጆቹም በሞት ሲወሰዱ በአቅመ ቢስነት ሸኝቷል፡፡ የእስራኤል ቦምብ የሞያ ባልንጀሮቹንም ነጥቆታል፡፡

ጣሪቅ አቡ አዙም የዕለት ተዕለት ውሏቸውን የሚዘግብላቸው ፍለስጤማዊያን ሰቆቃ የጀመረው እ.አ.አ ከ76 ዓመት በፊት በዛሬው ቀን ሜይ 15/1948 ነበር፡፡ በእስራኤል መሬታቸው በወረራ ተይዞ ጥቃት የሚፈራረቅባቸው ፍልስጤማዊያን፣ ይህን ቀን መቅሰፍት (“ነክበህ”) ብለው ይጠሩታል፡፡ በየዓመቱም ይታሰባል፡፡

በዚህ ወቅት አይሁዳዊያን በፍልስጤማዊያን ላይ ጦርነት ከፍተው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ቀያቸውን ጥለው እንዲሸሹ አድርገዋል፡፡ የቀጠለው ጥቃት የፍልስጤማዊያንን የሰባት ዐስርት ዓመታት ኑሮ ተቆጣጥሮት ሕይወታቸውን በሰቆቃ ሞልቶታል፡፡

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ፍልስጤማዊያን በመሬታቸው ላይ ለመንቀሳቀስ ጭምር ፍቃድ ሰጪው ሌላ ሆኗል፡፡ እስራኤል በተለይ ከ1995 ወዲህ በወረራ የያዘችውን ዌስት ባንክን በሦስት ሸንሽና በ700 ሺሕ ሠፋሪዎች ሞልታ ፍልስጤማዊያን በአንድ አካባቢ እንዲወሰኑ አድርጋለች፡፡ በዌስት ባንክ እስራኤል የራሷን ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ ስታሠፍር ከዐስር ሺሕ በላይ የፍልስጤማዊያን ግንባታዎችን አውድማ ነው፡፡

መሬታቸው ባዕድ የተወረረባቸው ፍልስጤማዊያን፣ ወደ ሥራ ሊሄዱ ሲሉ የይለፍ ፍቃድ ለማግኘት በማለዳ መሰለፋቸውም የዕለት ውሏቸው አካል ከሆነ ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ እስራኤል የፍልስጤማዊያኑ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ጥላ ሥማቸው በሥራ ፈትነት ከዓለም ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ሆኗል፡፡

እስራኤል የፍልስጤማዊያኑን ሰቆቃ የምታበረታው የንግድ እንቅስቃሴንም በማፈን ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ፍልስጤም ከአጎራባች ዐረብ ሀገራት ጋር የንግድ ግንኙነቷ ተቆርጧል፡፡ የወጪ እና ገቢ ንግዷም በእስራኤል በኩል እንዲያልፍ ጉልበተኛ ተሹሞበታል፡፡

እስራኤል በፍልስጤማዊያን ላይ የጣለችው ገደብ ወደ ቴክኖሎጂም የሚሻገር ነው፡፡ እስራኤል ለራሷ 5ጂ ኔትወርክ ስትጠቀም፣ ፍልስጤማዊኑ በ3ጂ ኔትወርክ እንዲወሰኑ ተደርገዋል፡፡ እስራኤል በገደብ የምትለቀውን ኔትወርክ ፍልስጤማዊያኑን ለመሰለል ጥቅም ላይ የምታውለው ነው፡፡ ፍልስጤማዊን የኔትወርክ ብቻ ሳይሆን የውሃ እና ሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች ላይ ገደብ ተጥሎባቸዋል፡፡

ለ76 ዓመታት በወረራ በያዘችው መሬት ላይ የተሾመችው እስራኤል፣ ከጥቅምት 2024 ወዲህ በንጹሐን ላይ የምትሰነዝረውን ሰብዓዊነት የጎደለው ጥቃት በመጠን አስፋፍታ ቢያንስ 35 ሺሕ ሰዎችን ገድላለች፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 15 ሺሕ የሚሆኑት ሕፃናት ናቸው፡፡ ፍልስጤማዊያኑ መቅሰፍት ሲሉ የሚጠሩትን የዛሬውን ቀን ሲያስቡ፣ በዓመታት ሰቆቃ ውስጥ ከአጠገባቸው የተለዩዋቸውን እያስታወሱ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular