በኢትዮጵያ የቤተሰብ ቀን በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ከተማ ተከብሮ ዋለ። ቀኑ ለሁለተኛ ጊዜ ሲከበር “መተሳሰብ እንደ ቤተሰብ፣ ለሀገርና ለማኅበረሰብ” በሚል መሪ ቃል ነው።
በዓሉ በተከበረበት መድረክ ላይ የቤተሰብን ሁለገብ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ለማሳደግ፣ ዕውቅና ለመስጠት እና ሁሉም ቤተሰብ፤ ለቤተሰብ አባላት ምሥጋና እና ክብር የሚሰጥበትን ዕድል ለመፍጠር በማለም መሆኑ ተገልጿል።
ቤተሰብ ትውልድን የመተካት፣ የልጆችን ሰብዕና የመቅረፅ፣ የሀገር ኢኮኖሚን የማሳደግ፣ ለቤተሰብ አባላት ዋስትና የመሆን ትልቅ ሚና ስላለው፣ ቤተሰብ ደኅንነቱ ሊጠበቅ እና ተገቢውን ክብር እንዲሁም ጥበቃ ሊያገኝ እንደሚገባም ክብረ በዓሉ በተሰናዳበት መድረክ አፅንኦት ተሰጥቶበታል።

በዛሬው መድረክ ላይ የተናገሩት በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ሕፃናት ዘርፍ ሚንስትር ዲኤታ ዓለሚቱ ዑመድ፣ ቤተሰብ የራሱን እና የአባላቱን ደኅንነት በመጠበቅ ለጤናማ ሀገር እና ማኅበረሰብ ምሥረታ መተኪያ የሌለው መሆኑን አብራርተዋል።
ሚኒስትር ዲኤታዋ በመልካም ሥነ ልቡና፣ በአካላዊ ጤንነት እና በኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይረጋገጣል ላሉት የቤተሰብ አባላት ደኅንነት መጠበቅ፣ ቤተሰብ እንደ ተቋም ቀዳሚ ድርሻ እንደሚወስድ አስታውሰዋል። የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የዛሬውን በዓል ባከበረበት ወቅት ሁሉንም ቤተሰብ አባላት ተጠቃሚ ያደርጋል ያለውን ለአንድ ዓመት የሚቆይ ዕቅድ ይፋ አድርጓል።
በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ የተከበረው የቤተሰብ ቀን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ30ኛ ጊዜ ተከብሮ አልፏል።












